Site icon ETHIO12.COM

ያራት ፊደል ስተት

ይድረስ
ለህይወት ፈጣሪ: እንዲሁም ለንጉስ ?
ጌታ ሆይ…ድምፅህን ስንሰማ፣ ጎናችን ነህ ብለን
በመፅናናት መንፈስ እንጎበኛለን፤
ደግሞም…
ድምፅህ ሲጠፋብን
የገዛ ስማችን እስኪረሳን ድረስ:ድንጉጥ እንሆናለን
ምክንያቱም
ስምህ ልባችን ላይ :የለም ኣልታተመም
ስምክን የነገሩን ስምህን ኣያውቁም።
እረኞች ያልካቸው: ፍፁም ከብት ሆነዋል
ሰባኮች ያልካቸው: ቀልድ ጀምረዋል
ክፉ ደግ የሚለይ …
ያማኞችህ ህሊና: ግኡዝ ነገር ሆኗል
ያለ መንፈስ ስጦት:
ያለ ዎይን መጎንጨት: ስካር ባገር በዝትዋል።
ይኸው እረኞችህ
ይኸው ሰባኮችህ:.
ያስደንጋጭ ቃላትን፤ በትር እያነሱ
ያንዲት ገፅን ሃሳብ፤ ባመት ሳይጨርሱ
በህይወት እውቀት ላይ እየተካሰሱ
በመዳን ሃሳብ ላይ እግር እያነሱ
ፍፁም ስጋ ለበስ :የድለላ ጥቅስን እየነሰነሱ
ቀልዶቻቸው መሃል ስምክን እያነሱ
ህንፃ ገንብተዋል ጎጆ እያፈረሱ።
ማለት ?
ልክ እንዳለም እውቀት
በሰላም ትርጉም ስም ጦር እንደሚጠራ
በረሃብ ማጥፋት ስም…
ይልቅ እንደሚሆን :ታላላቅ መከራ
ጌታ ሆይ ባንተም ስም
ባራት ፊደል ስተት ስንት ግፍ ተሰራ።
ስለዚህ ንጉስ ሆይ
ወይ ዉረድ
ወይ ፍረድ
ኣልያ…
ዝምታህ ከበዛ:ወደን ሳይሆን በግድ
ይመስለናልና
ኣንተም በእኛ ላይ ኣብረህ የምትቀልድ።
Ephrem Seyoum

via – addis admas

Exit mobile version