Site icon ETHIO12.COM

ጀርመን 80.6 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገባ፤ ትህነግ ሰላማዊ ዜጎችን ሰላም እየነሳና ተቋማት እያወደመ ስለሆነ እንዲወገዝ ተጥይቋል

የጀርመን መንግስት የ80.6 ፣ኢሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱ ተገለጸ። ይህ የሆነው የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከጀርመን የኢኮኖሚ ትብብርና የልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ከሆኑት ስቬኒያ ሹልሸ ጋር ከተወያዩ በሁዋላ ነው።

በዚህ ወቅትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የጀርመን መንግስት ከኢትዮጵያና ህዝቦቿ ጋር ላለው የማይቋረጥ የልማት ትብብር ምስጋና ማቅረባቸውን የመንግስት ሚዲያዎች ገልጸዋል።

የጀርመን መንግሥት ለኢትዮጵያ አዲስ የ80 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለመስጠት ቃል የገባው በትምህርት፣ ግብርና፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ እና አስተዳደር ዘርፍ ለመደገፍ ሲሆን፣ ድጋፉ ቀደም ሲል የነበረውን የሁለትዮሽ ግኑኝነት ትስስር በከፍተኛ መጠን የሚያሳድግ መሆኑ ተመልክቷል።

ወቅታዊውን የሀገሪቱን ሁኔታ በሚመለከትም በሰሜኑ የሀገሪቱ ከፍል የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ ውሳኔ እንዳሳለፈ አቶ ደመቀ ለሚኒስትሯ አስረድተዋል። ሆኖም ግን ከጠብ አጫሪ ባህሪው መላቀቅ ያልቻለው የህወሓት ቡድን አሁንም በአጎራባች ክልሎች ጦር እያዘመተ ጥፋት እየፈፀመ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

በዚህም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ዝምታውን በመስበር በሰብአዊ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተፅዕኖ ያሳደሩ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መሰረተ ልማቶችን በማውደም ህወሃትን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት ጠይቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እየደረሰ ያለውን አስከፊ ጉዳት፣ በህወሓት ምክንያት የተከሰተውን ግጭት እና በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ስላለው ድርቅ ሲናገሩም የጀርመን መንግስት የሚፈልገውን ሰብዓዊ እርዳታ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

አቶ ደመቀ ከሚኒስሯ ጋር በነበራቸው ቆይታም ጀርመን በኢትዮጵያ ስላለው ውስብስብ ሁኔታ ጥልቅ ግንዛቤ እንደሚኖራት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ዜና አቶ ደመቀ መኮንን ከስውዲን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ከአየርላንድ የውጭ ጉዳይና መከላከያ ሚኒስትር ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት አስረድተዋል።

የሀገራቱ ሚኒስትሮች በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቷ ሰላም እንዲሰፍን የወሰደውን አወንታዊ እርምጃ አድንቀው ይሄንንም እንደሚደግፉ ቃል ገብተዋል ሲል የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤትን ጠቅሶ ኢፕድ ነው የዘገበው።

Exit mobile version