ETHIO12.COM

‹‹አሸባሪው ህወሓት የጥፋት ባህሪውን የገለጸበት አፈትልኮ የወጣውን ሰነድ እየተገበረ ነው››

አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የወጠነበትንና ማንነቱን አስቀድሞ የገለጸበት ሰነዱን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ሰሞናዊ እንቅስቃሴው ማሳያ ነው ሲሉ ዶክተር አልማው ክፍሌ ገለጹ። 

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የህግና የታሪክ መምህር እንዲሁም የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ዋና ጸሐፊ ዶክተር አልማው ክፍሌ የአሸባሪውን ወቅታዊ እንቅስቃሴ አስመልክተው ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የአሸባሪው ህወሓት የጥፋት እንቅስቃሴ የተጠናና የተደራጀ መሆኑ አፈትልኮ በወጣው ባለ 82 ገጽ ሰነድ ላይ መቀመጡን አስታውቀዋል። የሽብር ቡድኑ አገርን የማፍረስ ግቡን ለማሳካት የወጠነበት ሰነዱን አሁን ላይ እያደረገ ባለው እኩይ ተግባሩ ተፈጻሚ እያደረገው እንደሆነ አመላክተዋል። 

የአሸባሪው ቡድን አገርን ለማፍረስ የራሱ የሆነ ስትራቴጂ እንዳለው የገለጹት ዶክተር አልማው፤ ብጥብጥ መፍጠር፣ ከተሞችን ማቃጠል፣ ድርድር፣ ሌሎች ብሄረሰቦችን ማነሳሳት፤ እንደርሱ ያሉ የጥፋት ኃይሎችን አደራጅቶ በየቦታው ፍንዳታና አመጾች መፍጠር የሚሉት ከሽብር ቡድኑ አፈትልኮ በወጣው ሚስጥራዊ ሰነድ ላይ መካተታቸውን አስታውሰዋል። 

እነዚህን አማራጮችን እየተጠቀመ ማንነቱን አስቀድሞ የገለጸበትና አፈትልኮ የወጣውን ሰነዱን በተግባር ላይ እያዋለው ይገኛል ብለዋል። እንደ ዶክተር አልማው ገለፃ፤ የሽብር ቡድኑ ሰነዱን ተግባራዊ እያደረገ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ያሏቸውን በሻሸመኔ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአጣዬ፣ በወሎ፣ በሸዋ ውስጥ የተፈጠሩትን ክስተቶች ለአብነት ጠቅሰዋል። 



በአሁኑ ወቅት የወንበዴ ቡድን እያሰማራ ከተሞችን መዝረፉ፣ ሰዎችን መግደልና ማፈናቀሉም የሰነዱ አንዱ አካል እንደሆነ ጠቅሰዋል። ከዚህም ባሻገር አሸባሪው ጠላትን የመገርሰስ ስትራቴጂዎች እና የማስፈፀሚያ ስልቶች እና አቅጣጫዎች ብሎ ሰነዱ ላይ እንዳስቀመጠው “ትግራይን አንጠፍጥፎ ማዘጋጀት” የሚለው ሀሳብ ተጠቃሽ ሲሆን፤ የትግራይ ህዝብ አስገድዶ ለዚሁ ጦርነት እየማገደ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

ህዝቡን እንደመያዣና ጋሻ አድርጎ መጠቀም የጀመረው አሁን አይደለም ያሉት ዶክተር አልማው፤ የህዝቡ እስትንፋስና መንፈስ እንዲሁም የእነርሱ ህልውና እንደሆነ በተለያየ መንገድ ከ40 ዓመታት በላይ ሰርቷል ብለዋል። አሁንም የትግራይ ተወላጆችን አስጨንቆ እየገደለ፣ በጅምላ እየጨረሰና እየቀበረ እንዲሁም እየቀማ “ትግራይን አንጠፍጥፎ መጠቀም” የሚል በሰነዱ ውስጥ አካትቶ እየታገለ ነው ሲሉ ተናግረዋል። በሁለት ክፍሎች የተደራጀው የአሸባሪው ሰነድ አፈትልኮ ይውጣ እንጂ ቡድኑ አጥፊ ስለመሆኑ ከመጀመሪያው ጀምሮ ይታወቃል ብለዋል።

እኛ አገር ካልመራን እናፈርሳለን ብለው ያደረጓቸው በርካታ እንቅስቃሴዎች ማሳያ እንደሆኑ ገልጸዋል። በህልውና ዘመቻው በዚህ አጥፊ ኃይል ላይ እስከመጨረሻው የማያዳግም ርምጃ ካልተወሰደ እንዲህ ያሉ እኩይ ተግባሩ እንደማያባራ ዶክተር አልማው ገልጸዋል። በመሆኑም የጀመረውን አጥፊ የሰነዱን እንቅስቃሴ ማክሸፍና ግብዓተ መሬቱን ማፋጠን አንደሚገባ አሳስበዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2014

Exit mobile version