Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ ቀልብ ከገዛና የሰላም መንገድ ካለ መንግስት ዝግጁ መሆኑንን አስታውቀ፤

የፌደራል መንግሥቱ ከህወሓት ጋር ድርድር እያደረገ ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “እስካሁን ደቂቃ ድረስ ድርድር አልተደረገም። ድርድር አላደረግንም ማለት ግን እስከናካቴው ድርድር አይኖርም ማለት አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ለሰላም አማራጮች የሆኑ መንገዶች እንደሚወሰዱ ጠቁመው “የሰላም አማራጭ ካለ፣ ህወሓት ቀልብ ከገዛ በደስታ እናየዋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ትላንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገር ምክክር ኮሚሽነሮች መመረጣቸውን አጣቅሰው “እኔ ድርድር ብዬ የማስበው አገር አቀፍ ውይይቱን ነው” ብለዋል።

በምክር ቤቱ የጸደቁት 11 ኮሚሽነሮች ሚናቸው “ሁሉንም ማኅበረሰብ ማወያየት ነው እንጂ በሕዝበ ውሳኔ የሚወስነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው” ሲሉም አክለዋል።

“እስካሁን ደቂቃ ድረስ ከህወሓት ጋር ድርድር አልተደረገም። ድርድር አላደረግንም ማለት ግን እስከናካቴው ድርድር አይኖርም ማለት አይደለም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምላሽ ሰጡ።

በዛሬው ዕለት የካቲት 15፣ 2014 ዓ. ም. በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም የመንግሥታቸው የስድስት ወራት አፈጻጸም በተመለከተ ማብራሪያ ሲስጡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የፌደራል መንግሥቱ ከህወሓት ጋር ድርድር እያደረገ ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ነው ይህንን ምላሽ የሰጡት።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል እየተካሄደ ነው ስለሚባለው ድርድር ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

በተለይም ህወሓት በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ ከመፈረጁ አንጻር ድርድሩ፣ ከሞራል፣ ከሕጋዊነት እና ቅቡልነት አንፃር እንዴት ይታያል? የሚልም ጥያቄ በማቅረብ ማብራሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይስጡኝ ብለዋል።

በተጨማሪም በቅርቡ መንግሥት የእነ አቶ ስብሃት ነጋን ክስ ማቋረጡ ከሕግ አግባብ ውጭና ሕገ መንግሥቱን የሚጣረስ ነው በሚል ውሳኔው እንዲቀለበስና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

በሦስተኛው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባሎች የቀረቡላቸውን ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሁለት ከፍለው ምላሽ ሰጥተዋል።

ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች፣ በአፋር ክልል እንደ አዲስ ያገረሸው ጦርነት፣ የእስረኞች መፈታት፣ ከህወሓት ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር፣ የሻከረው ዲፕሎማሲ፣ የልዩ ኃይሎች መዋቅር እንዲሁም በአምባሳደሮች ሹመት ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።

ስለ እስረኞች መፈታት

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም ስለእነ አቶ ስብሃት ነጋ ክስ መቋረጥና እስረኞች የተፈቱበትን ምክንያት እንዲያብራሩ ከብዙ የምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ እስረኞች የተፈቱት “እኛ የሞራል ልዕልና ስላለን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

“እኛ የሞራል ልዕልና አለን። እናፈርሳቸዋልን፣ እንገድላቸዋለን ላልናቸው ምሕረት መስጠታችን የሞራል ልዕልና ይሰጠናል። ጉዳት የለውም” ሲሉ ውሳኔውን አስረድተዋል።

አያይዘውም “ጠላቶቻን በቀየሱልን መንገድ መጓዝ አሸናፊ አያደርገንም። እኛ ለድል የሚያበቃንን መንገድ መቀየስ አለብን” ብለዋል።

እስረኞችን ለመፈታት የወሰኑት በሦስት ምክንያቶች እንደሆነ ጠቅሰው “አንደኛው ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና የጋራ ቤት ለመሥራት ነው” ብለዋል።

ጨምረውም “ሁለተኛውም ምክንያት የታሳሪዎችን ሁለንተናዊ ሁኔታ ያገናዘበ ነው። ሁሉም እስረኛ አይደለም የተፈታው። ሦስተኛው ምክንያታችን ያገኘውን ድል ለማጽናት ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

እስረኞችን ክስ አቋርጦ መፍታት ሕጋዊ ተቃርኖ የሌለው ውሳኔ እንደሆነ ጠቅሰው “በእርስ በእርስ ጦርነት ፍፁም ድል የለም። እኛ የምንመርጠው በቂ ድል ነው። አገርን ለመታደግ ነው” ሲሉ እስረኞች የተፈቱበት ምክያት አስረድተዋል።

አያይዘውም “እነዚህ ሰዎች በመፈታታቸው ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ናት። የፈታናቸው በጉቦ፣ በዝምድና አይደለም። የመፈታታቸውን ጥቅም አይተነዋል” ብለዋል።

ድርድር እየተደረገ ነው?

የፌደራል መንግሥቱ ከህወሓት ጋር ድርድር እያደረገ ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “እስካሁን ደቂቃ ድረስ ድርድር አልተደረገም። ድርድር አላደረግንም ማለት ግን እስከናካቴው ድርድር አይኖርም ማለት አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ለሰላም አማራጮች የሆኑ መንገዶች እንደሚወሰዱ ጠቁመው “የሰላም አማራጭ ካለ፣ ህወሓት ቀልብ ከገዛ በደስታ እናየዋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ትላንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገር ምክክር ኮሚሽነሮች መመረጣቸውን አጣቅሰው “እኔ ድርድር ብዬ የማስበው አገር አቀፍ ውይይቱን ነው” ብለዋል።

በምክር ቤቱ የጸደቁት 11 ኮሚሽነሮች ሚናቸው “ሁሉንም ማኅበረሰብ ማወያየት ነው እንጂ በሕዝበ ውሳኔ የሚወስነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው” ሲሉም አክለዋል።

ብሔራዊ ውይይት

ይህ ብሔራዊ ውይይት በቀላሉ መታየት እንደሌለበትና የተቃዋሚ ፖርቲዎችም ዕድሉን መጠቀም እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።

“ለህወሓትም ሆነ ለየትኛውም ኃይሎች” ትናንት የጸደቁት ኮሚሽነሮች ዋነኛ ተግባራቸው መድረኮችን ማመቻቸትና አጀንዳዎችን መፍጠር ነው ብለዋል።

በአፍሪካ ውስጥ በአብዛኛው የሚደረገው የልሂቃን ውይይት እንደተደረገና ይህ ደግሞ አገራዊ አጀንዳ ሳይሆን ሥልጣን ክፍፍል መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት አገሪቷ የምትዘጋጅበት ውይይትም ሆነ ድርድር የሥልጣን ክፍፍል አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል ብለዋል።

የሥልጣን ክፍፍሉ በምርጫ የተጠናቀቀ ጉዳይ ነው ብለው፤ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያን የሚገዛት ብልፅግና ፓርቲ መሆኑን አስታውሰዋል።

ብሔራዊ ውይይቱና ምክክሩ የሚደረገው በቆሰሉ ታሪኮችና ነገ በምንገነባት ኢትዮጵያ ላይ ፟እንደሆነ “የምንገነባው አገር ከሥልጣናችን በላይ ስለሆነ ነው፤ ለወደፊቱ ትውልድ ስለሆነ ነው” ሲሉም አስረድተዋል።

የውይይቱ ሂደት በዋነኝት ሊያካትታቸው የሚገባ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰው ይህም ግልፅ፣ የሚገለል ማኅበረሰብ የሌለበትና ሁሉንም ሕዝብ አሳታፊ ሊሆን እንደሚገባም አንስተዋል።

እንደ ምሳሌ የጠቀሱት በሕገ መንግሥቱ ላይ ያለውን አንቀፅ 39፣ በርካታ ጥያቄ የሚያነሱ ፓርቲዎችን ጉዳይ እንዲሁም የሰንደቅ አላማ ጉዳይን ሲሆን በአሁኑ ወቅት አገሪቱን የሚያከራክሩና የሚያጣሉ ጉዳዮች መቋጫ ሊያገኙ የሚችሉበት ነው ብለዋል።

ውይይት የሚያስፈልገው ሽኩቻ፣ ጦርነትና የፖለቲካ ሽግግር ሲኖር መሆኑን ጠቅሰው አገሪቷ እያተዘጋጀችበት ያለችውም ምክክር አራት ምዕራፎች እንዳሉት ጠቅሰዋል።

እስካሁን የተካሄደው ቅድመ ዝግጅት ሲሆን እስካሁን ያለው ብሔርና ፆታን ባሳተፈ መልኩ የተዋቀረ በመሆኑ ጥሩ ጅማሮ ነው ብለዋል።

“በውይይትና በድርድር የሚፈታ ችግር ካለ መንግሥት ለማንም በሩ ክፍት ነው። እኛ የምንጠላው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚነካ ሲሆን ነው” ብለዋል።

በጦርነቱ ለተጎዱት አማራና አፋር ክልሎች በጀት

በጦርነቱ የተጎዱትን የአማራና የአፋር ክልሎች መልሶ ለማቋቋም የተመደበው በጀት አነስተኛ ነው በሚል ከምክር ቤት አባላት ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

የሁለቱን ክልሎች ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ሕዝቦች ችግር መጠቀስ አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የትግራይ ሕዝብ መብራት የለውም፣ ምግብ እየተቸገረ ነው፣ መድኃኒት እጥረት ላይ ነው” ብለዋል።

አክለውም “ትግራይ እንድትገነጠል አንፈልግም፤ ትግራይ ትገንጠል ብትባል 100 ፐርሰንት አይሆንም ትላላችሁ። እንዲገነጠሉ የማንፈልግ ከሆነ እንዳይጎዱም ስለ ሕዝቡ የሚገባውን መብት ማሰብ አለብን። ያንን ማድረግ ከቻልን ነው አብረን ነው መኖር የምንችለው” ብለዋል።

በተጨማሪ በሰሞኑ እንደ አዲስ ካገረሸው ጦርነት ጋር ተያይዞ የአፋር ክልል በፌደራሉ ወይም በመከላከያ ተዘንግቷል በሚል ከምክር ቤት አባል ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በምላሹ የፌደራል መንግሥት ከአፋር ክልል ጋር በከፍተኛ ቅርበት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

“ማንኛውም የአፋር ጥቃት፣ የአማራ ጥቃት የኢትዮጵያ ጥቃት ነው” በማለትም የሰሞኑ ጥቃት አላማ አፋር አይደለም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በትግራይና በአፋር ክልል የተነሳውን ጦርነት ህወሓት “የእርዳታ እህል እንዳይገባ በሚል ነው ጥቃት የከፈተው” ብለውታል።

የአማራና የአፋር ክልሎች ወደ ትግራይ እርዳታ እንዳይገባ ዘግተዋል የሚባለውም ከእውነት የራቀ እንደሆነም አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ መንግሥታቸው የትግራይን ሕዝብ ሆን ብሎ እንደሚያስርብና እርዳታ እንደሚከለክል እንደሚታሰብም ገልጸዋል። “ስማችን በዓለም ላይ ጠልሽቷል፤ እኛ ሕዝብ እንዲራብ አንፈልግም” ብለዋል።

በዚህ ጦርነት እንደ ትግራይ ክልል የተጎዳ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራና የአፋር ሌላውም ኢትዮጵያ ትግራይን መገንባት እንዳለበትም አስረድተዋል።

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለውና መንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚለውን ቡድን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “ኃይሉ አላማ የሌለው፣ ዘረፋና ግድያና የሚፈፅም” መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ኃይልም ለመግታት መንግሥትና የኦሮሚያ ክልል ለወራት ያህል ከፍተኛ መስዋዕትነት እንደከፈሉ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ላይ ከፍተኛ መሠረተ ልማቶችን ቢያወድምና መንግሥትም ኃይሉን ለመግታት ከፍተኛ ሥራ ቢሠራም “በወታደራዊ ሥራዎች ብቻ የሚፈታ አይደለም። ሕዝቡስ ለምን ተሸከመው? ለምን ቀለበው? የሚለው ጥያቄ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ መፈታት አለበት” በማለት አስረድተዋል።

ሆኖም የትኛውም ታጣቂ ኃይል “ኢትዮጵያን አያሸንፍም” ብለዋል።

ልዩ ኃይል

የልዩ ኃይል አወቃቀር ላይ የተነሳውን ጥያቄ በተመለከተ በየክልሉ ያለውን ችግር ለመፍታት ልዩ ኃይል አስፈላጊ እንደሆነና የልዩ ኃይል አባላት እንዴት ይሥሩ? የሚለው ላይ ግን ንግግር በማድረግ ለወደፊት አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚቻል ተናግረዋል።

የተቃዋሚዎች ተሳትፎ

የምክር ቤቱ አባላት ካነሱት ጥያቄ መካከል መንግሥት ምን ያህል ከተቃዋሚዎች ጋር ይሠራል? የሚለው ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምላሻቸው የአገር ምክክር ኮሚሽን በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚኖረውን መናበብ የተሻለ ያደርጋል ብለው እንደሚያምኑ ጠቁመዋል።

እስካሁን ድረስ በነበረው ሂደት “የልሂቃን አክራሪነት እጅግ አደገኛ ነው። ዋልታ ረገጥነት አገርን ይጎዳል” ሲሉ አጠቃላይ የፖለቲካ ልሂቃል ግምገማቸውን አስቀምጠዋል።

ድርቅ

በሶማሌ፣ ኦሮሚያና ሌሎችም በአገሪቱ በተለያዩ ክልሎች የተስፋፋውን አሳሳቢ ድርቅ በተመለከተ ምላሽ ሲሰጡ “እስካሁን ሰው አልሞተብንም” ብለው እስካሁን 750 ሺህ ኩንታል ምግብን ጨምሮ የልጆች ምግብ፣ የከብት መኖ እና ክትባት እንደተላከ ጠቅሰዋል።

ግድቡ

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨትና ከሱዳን እንዲሁም ከግብፅ ጋር ያለውን ውጥረት በተመለከተ “ውሃው ተርባይኑን መትቶ ሄዷል። ከዚህ በኋላም በድርድርና በውይይት አብረን እንሠራለን” በማለት ኢትዮጵያ ሦስቱንም አገራት ያማከለ አካሄድ እንደምታራምድ ተናግረዋል።

ዲፕሎማቶች ሹመት

በአገሪቱ ውስጥ አነጋጋሪ የተባሉት የሁለቱ ጄኔራሎች ባጫ ደበሌና ሃሰን ኢብራሂም እንዲሁም የኢንጂነር ስለሺ በቀለ በአምባሳደርነት የተሾሙበት መስፈርት ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

በተለይም በቅርቡ የተሰጡ የአምባሳደር ሹመቶችን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ብቃት ያላቸው ሰዎች ናቸው የተሾሙት” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

“በኢትዮጵያም በዓለምም ብዙ ወታደር አምባሳደር አለ። ውጊያ መምራት እና ዲፕሎማሲ ተመጋጋቢ ነው” በማለት ሹመቶቹ በምን ምክንያት እንደተሰጡም ጠቁመዋል።

ሳዑዲ ያሉ ኢትዮጵያውያን

በሳዑዲ አረቢያ በተለይም በእስር ቤቶች የሚንገላቱ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፤ ሁሉም ሳዑዲ ያሉት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመለሱ ያደረገው ምክንያት ከመካከላቸው “የሠለጠኑ ገዳዮች” እንዲሁም በሌላ መንገድም የደኅንነት ስጋት የሆኑ ስላሉበት እንደሆነ አስረድተዋል።

“ከሳዑዲ ጋር በቅርበት እየሠራን ው። ስንመልሳቸው ጥፋት የሚያስከትሉ እንደሚኖሩ ስጋት ስላለብን ነው። አብረው የሚጎዱ ንጹሀንም ስላሉ ጥናት እያደረግን ነው” ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሙሉ ዘገባው የቢቢሲ ነው፤ እርዕስ የተቀየረ

Exit mobile version