ከ”ልሂቃን” በተጨማሪ፣ ትህነግ “የሰሊጥ ፖለቲካን” ከሰላም መንገድ እንቅፋቶች አንዱ አደረገ፤ ” ወሮ ሰሊጥ ማፈስ አክትሟል”

የትግራይ አጋርነት ፅ/ቤት ዋና ዳሬክተር አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው መንግስትን “ሰላም ፈላጊና፣ የማይፈልጉ” ሲሉ በመክፈል ሲናገሩ ለሰላም መንገድ እንቅፋት ካሉዋቸው ልሂቃን በተጨማሪ የሰሊጥ ፖለቲካ እንደሚገኝበት አስታወቁ። ትህነግ የማይደራደርባቸው ጉዳዮች አሉ ማለት መነጋገር አይቻልም ማለት ግን እንዳልሆነ አመልከቱ። ኢትዮጵያ አሜሪካ የምትፈልገውን ካላደረገች ግንኙነታቸው እንደሻከረ እንደሚቀጥል አመለከቱ። “አገር በጉልበት ወሮ ሰሊጥ ማፈስ አክትሟል” ተባለ።

ከትግራይ በሚሰራጭ የትግራይ ቲቪ ዩቲዩብ ገጽ ላይ ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት አቶ ወንድሙ ለሰላም በመንግስት በኩል መልካም ጅማሬዎች መኖራቸውን አመልክተዋል። ድርድር ስለመጀመሩ ቁርጥ አድርገው አልተናገሩም። ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርድር ብሎ ነገር አልተደረገም ላሉት ምላሽ አልሰጡም።

አብን፣ ባልደራስ፣ እናት ፓርቲ፣ አማራ ብልጽግናን በስም በመጥራት፣ ሌሎች ከልሂቃን ጋር የተመደቡ አንቂዎችን በማከል የሰላም ሂደቱ ጠንቅ እንደሆኑ አቶ ወንድሙ አመልክተዋል። የወልቃይት ጠገዴ ለም መሬትን በስም ሳያነሱ “የሰሊጥ ፖለቲካውም አለበት” ሲሉ ከዚሁ ሃብት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ወገኖች ሰላሙን እንደምያፈልጉት ገልጸዋል። ሲያጠቃልሉዋቸው ደግሞ ” የድሮዋ ኢትዮጵያ ናፋቂዎች፣ የተስፋፊነት ስካር ያልለቀቃቸው” ብለዋቸዋል። በስም ባይገልጹም የወልቃይት ጠገዴ መሬት ጉዳይ ስለመሆኑ የሚታወቅ ነው።

ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ሰላም እንዳይሰፍን በዋናናት ምክንያት የሆኑት የኤርትራው መሪ እንደሆኑ ከዲፕሎማሲው ቋንቋ በዘለለ ያስረዱት አቶ ወንድሙ፣ “የኢሳያስ ጉዳይ እኛን አይመለከትም፣ በድርድሩ የለበትም። ከነሱ ጋር የምንነጋገረው በሌላ ቋንቋ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። ኢትዮጵያ ግን ኤርትራን ልታገል እንደሚገባት አመልክተዋል። ኢትዮጵያ ኤርትራን እንድታገል ሲመክሩ “ታላቋ ትግራይ” ለመመስረት ድርጅታቸው የኤርትራን ደጋማ አካባቢዎችና ቀይባህርን የመጠቅለል ዕቅዱን ከአስተያየታቸው ጋር እንዲያስማሙ አልተጠየቁም።

“ከማንም በላይ ኢትዮጵያዊ ናቸው። በባንዲራ ተጠቅልለው ሲታዩ ኢትትዮጵያን ከነሱ በላይ የሚወድ ያለ አይመስልም” ሲሉ በሊህቃን ጥላ ስር ያስቀመጡዋቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያን ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል እንደዳረጉዋት አድርገው አቅርበዋል።

አወያይዋ የመናገሪያ ርዕስ እንጂ፣ ጥያቄ በማታቀርበበት የንግግር ክፍለ ጊዜ “ጦርነት መጣብን እንጂ ወደ ጦርነት አልሄድንም” በሚል በተደጋጋሚ ሲገልጹ የተሰሙት አቶ ወንድሙ፣ የትህነግ ሃይል ንፋስ መውጪያን ተሻግሮ፣ ደሴን ተሻግሮ ሸዋ፣ አፋርን ተሻግሮ ወደ ጭፍራና ሚሌ ለምን ተግባር እንደተሰማራ አልገለጹም። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን በመብረቃዊ ጥቃት በ45 ደቂቃ ውስጥ መበታተኑንን በኩራት ላስታወቀው የድርጅታቸው ልሳንና አመራሮች ምስክርነት ማስተባበያም አላቀረቡም። የጦርነቱ መነሻ የአገር መከላከያ መሆኑንን አሜሪካ ሳትቀር ማመኗን አላነሱም። “ወደ ጦርነት አልሄድንም” በሚሉበት ሰዓት አፋር ላይ የትህነግ ሃይል ከሶስት መቶ ሺህ ሕዝብ በላይ ማፈናቀሉንና በርካቶችን በካባድ መሳሪያ እየጨረሰ ስለመሆኑ ያሉት ነገር የለም።

በንግግራቸው ሌላው ያነሱት ኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነታቸው ምንም መሻሻል እንዳላሳየ ነው። ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ የምትፈልገውን ካላደረጉ ግንኙነቱ እንደሻከረ ይቀጥላል” ብለዋል። በመስከረም 3 ቀን 2020 Core Digital Woyane “በማንኛውም ዘመን አሜሪካኖች ዲሞክራሲያዊ ሆኖው አያውቁም።ሰብአዊ ፍትሃዊ ሆኖው አያውቁም።በአገር ውስጥ ዲሞክራሲያውያን ናቸው። ወዳጅ ታዛዥ ከሆንክ እንደ ሳዑዲ ዓረብያ ንጉስ ልትሆን ትችላለህ ። ስለ ምርጫ እማይነሳበት የማይታሰብበት አገር ልትሆን ትችላለህ፤ ወዳጃቸው ከሆንክ ተላላኪ ከሆንክ” ሲሉ ጽፈው ነበር።

ይህን ብለው የነበሩት ዲፕሎማቱ አቶ ወንድሙ የኢትዮጵያ መንግስት አሜሪካንን “እሺ፣ አዎ፣ አደርጋለሁ፣ ምን ልታዘዝ” ማለት እንዳለበት ሲያስታውቁ ከላይ ካሉት በተቃራኒ የኢትዮጵያ መንግስት ይላላክ፣ አሽከር ይሁን ለማለት አስበው እንደሆነ አላብራሩም። በእሳቸው እየታ ግን ድርጅታቸው ትህነግ ለአሜሪካ የማይንበረከክ፣ የማይታዘዝና የማይላላክ እንደነበር በጹሁፋቸው አመልክተዋል።

በዚሁ “የሰላም ዕድልና ፈተናዎቹ” በሚል ርዕስ ከአወያይዋ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰማይና የምድር የእርዳታ ፈቃድ መሰጠቱን አመስግነዋል። ጅምሩ ሊሻሻልና ሊሰፋ እንደሚገባም አመልክተዋል። መተማመንን ለመፍጠር እንደሚረዳ ገልጸዋል። አያይዘውም የጠቀሷቸው አካላት እንቅፋት ቢሆኑም የሰላም እድል እንዳለ ግን ደጋግመው አንስተዋል።

ብልጽግና በሰላም ጉዳይ ለሁለት የተከፈለ አድርገው ያስቀመጡት እኚሁ የትህነግ ሹም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ነጥለው በማውጣት ንግግራቸውን ለዚሁ የተከፍለዋል አሳብ መደገፊያ አድርገውታል። በአንድ ጎን አድነቀው መልሰው በትግራይ ለተፈጸመው ወንጀል በዓለም ዓቀፍና በአገር ውስጥ ሕግ ተጠያቂ ከመሆን እንደማያልፉ፣ ዛሬ ላይ የደረሱት ጦርነት እንደማያዋታቸው ተረድተውና ተሸንፈው እንደሆነም ገልጸዋል።

የትህነግ ሃይል የተሰጠውን የመጨረሻ እድል አልጠቀምበት ማለቱን መንግስት በተደጋጋሚ ሲያስታውቅ መቆየቱ፣ ሰራዊቱ ሰፊ የማገገምና ዳግም የመደራጀት ተግባር አጠናቆ ለአስፈለጊ ግዳጅ በዝግጅት ላይ እንደሆነ፣ ይህንኑ እድል መተቀም ባለመቻሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድበት ጫፍ ላይ መድረሱን የጦር ሃይሎች ኤታማዦር ሹም በይፋ ሰመራ ላይ ተናገረዋል።

ዲፕሎማቱ “አስገድደንና አሸንፈን” ሲሉ መንግስት የድርድር አሳብ እንዲይዝ ማድረጋቸውን ቢገልጹም የትግራይ ወጣቶች ማህበር ሰላሳ ሺህ የሚሆኑ የትግራይ ወጣቶች የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ ማስታወቁ ይታወሳል። በሁለት ሳምንት ውስጥ ከወረራቸው አካባቢዎች ” መውጣት እንደመግባት ቀላል አይደለም” በሚል መፈክር ስለተካሄደው ኦፕሬሽንና ውጤቱ ያሉት ነገር የለም። ” ማሸነፍ” ሲባልስ ምን ማለት እንደሆነ አላብራሩም።

“የሰሊጥ ፖለቲካ” ላሉት አንድ ከፍተኛ የአማራ ብልጽግና አመራር ” በሃይል ወሮ ሰሊጥ ማፈስ ድሮ ቀረ። እሱ አክትሟል። ኮሎኔል ደመቀ ምላሹን በግልጽ ሰጥቷል። እሱ የመንግስት አቋም ነው። በግፍ የተነጠቅነውን መሬት፣ በሃይል አስመልሰናል። ሰሊጥ ፖለቲካነቱ ለትህነግ እንጂ ለኛ ተፈትሮ በሰጠን ሃብታችን ላይ በእምነት ዘርተን የምናፍሰው ነዳጃችን ነው።” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል። የአካባቢውን ህዝብ ይበልጥ ማናገሩ እንደሚጠቅም አመልክተዋል። አያይዘውም የሕዝብን ስሜትና ፍላጎት ማክበር ግዴታ መሆኑንንም አመልክተዋል።

በሚታወቁ የትግራይ ተወላጅ ተቆርቋሪዎች የሚወጡ መረጃዎች በትግራይ ሰላማዊ ዜጎች ስቃይ ላይ ናቸው። እርቅና ሰላም አስፈላጊ ነው። ይህን አስፈላጊ ጉዳይ ሁሉም ወገን በአሸናፊነት በሚወጣበት አግባብ ከሕዝብ ጥቅም አንጻር መቋጨት እንደሚገባ ይታመናል። ወንድሙ አሳምነው “ሁሉም ይንከባከበው” እንዳሉት ከቅጥፈትና ከተራ የፖለቲካ ድራማ በመውጣት ሰላም ማስፈን አማራጭ የለውም።

Related posts:

«ሕወሓት ጦርነትን እንደ አምልኮ የሚቆጥር ቡድን ነው» – ፕሮፌሰር ሀረገወይን አሰፋ
«በሕገወጦች ላይ ያለ ምኅረት እርምጃ መውሰድ አለብን፤ ይህ የመንግሥት ተግባር ነው» የአማራ ክልል
125 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ
«በአገሩ መከላከያ ላይ አፉን የሚከፍት ሕዝብ የለም፤ መንግስትም አይታገስም» ክብር ለመከላከያ ሰራዊት!!
በኢትዮጵያና ቱርክ መካከል የተደረገውን የወታደራዊ ማዕቀፍ ስምምነት ምክር ቤቱ አጸደቀ
የሞት ፍርደኛው የ25 ዓመታት ሰቆቃ! ከመሬት በታች የታፈኑት አባት
«ኢትዮዽያን ማስቀጠል ከሚፈልጉት ጎን በመሆናችን የሚከፋ ከአለ እርሱ መፍረሷን የሚናፍቅ ብቻ ነው!»
ደብዳቤ ለኢትዮጵያ - ከቢልለኔ ስዩም
የዓለም ባንክ የ300 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ፈረመ
"እናቴ ፍጹም እስር ቤት እንድትገባ አልፈግም" ብሎ እግሩን ያጣው ወጣት ምስክርነት ለሮይተርስ
"አልዘምትም" ወይም "ከጠላት ጎን እሰለፋለሁ" ማለት ሲቻል ማውሰብሰብና ማድበስበስ አይገባም!
አብዱላሂ ፋርማጆ ለአዲሱን ፕሬዝዳንት «ሁሉም ወገኖቼ እንዲደግፉህና እንዲጸልዩልህም እጠይቃለሁ»
መንግስ የጸጥታ ሃይሎች ለየትኛውም ዓይነት ትንኮሳ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ማድረጉን አስታወቀ
በትግራይ 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ ዕርዳታ እየደረሰ ነው፤ ከሺህ በላይ የጭነት መኪኖች ታግተዋል፤ 76 ቢሊዮን ብር ወደ ትግራይ ተልኳል
የደህንነት ጥናት አዲሱ ምዕራፍ - ጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ

Leave a Reply