Site icon ETHIO12.COM

በእነ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ – የስር ፍርድ ቤት የፈቀደውን የዋስትና መብት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሻረው

ዐቃቤ ህግ በዋስትና ሊለቀቁ አይገባም በሚል ይግባኝ የጠየቀባቸው በእነ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ የተከሰሱ የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ሰራተኞች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን አንዲከታተሉ ተወሰነ

ለተከሳሾች የስር ፍርድ ቤት የፈቀደላቸውን የዋስትና መብት የሻረው በጠቅላይ ፍርድ ቤት 1ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ነው።

በቀድሞው የመረጃና ብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንንነት ቢሮ ምክትል ዳሪክተር አቶ ያሬድ ዘሪሁን ጨምሮ የተቋሙ የፀረሽብር ጉዳዮች መምሪያ ሀላፊ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ 22 ተከሳሾች የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጉዳያቸውን ሲከታተል ለቆየው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የዋስትና መብት ጠይቀው በአንድ ዳኛ የድምጽ ተቃውሞ በሁለት ዳኞች አብላጫ ድምጽ ተከሳሾቹ ክሳቸውን እንዲከላከሉ በተባለበት በተሻሻለው አንቀጽ 423 እና አንቀጽ 556 መሰረት ሁሉም ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ 30 ሺህ ብር ዋስ አስይዘው ከእስር እንዲፈቱና ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ ብይን መስጠቱ ይታወሳል ።

በዚህም መሰረት ዐቃቤ ህግ ተከሳሾች ተደራራቢ ክስ እንዳለባቸው፤ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዋስ ከወጡ በቀጣይ ቀጠሮ ግዴታቸውን አክብረው የማይቀርቡ መሆኑን በመግለጽ የተከሳሾች በዋስትና መፈታት አግባብ አለመሆኑን የያዘ ባለ ዘጠኝ ነጥብ ምክንያቶችን ጠቅሶ በተከሳሾች ዋስትና ላይ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 1ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት መቃወሚያ በማስገባቱ ይታወሳል፡፡

የተከሳሽ ጠበቆች ተከሳሾቹ ይከላከሉ የተባሉበት አንቀጽ ዋስትና የማያስከለክል በመሆኑ የስር ፍርድ ቤቱ ዋስትና መፈቀዱ የህግ አግባብ ያለው በመሆኑ የተፈቀደው የዋስትና መብት ይጽናልን ሲሉ መከራከሪያ ነጥቦችን ጠቅሰው መልስ ሰጥተዋል።

መዝገቡን የመረመረው በጠቅላይ ፍርድ ቤት 1ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ በዛሬው የካቲት 16/2014 ዓ.ም በአስቻለው ችሎት የዋስትና ውሳኔውን በመሻር በሁለት አብላጫ ድምጽ በአንድ ዳኛ ልዪነት ተከሳሾቹ ከነበራቸው ስልጣን አንጻር በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ አንቀጽ 67/ሀ መሰረት የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታን ከግምት በማስገባት ተከሳሾች በዋስ ቢወጡ ግዴታቸውን አክብረው ችሎት ላይቀርቡ ይችላሉ ሲል የዐቃቤ ህግ ይግባኝ ተቀባይነት አግኝቶ ዋስትናውን ሽሮታል።

ተከሳሾች ሰዎችን ያለአግባብ በማሰር የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ተብለው ክስ የቀረበባቸው በእነ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ በማረሚያ ቤት የሚገኘው ያሬድ ዘሪሁንና ሌሎች 24 ተከሳሾች ላይ እንደየጥፋተቸው በፈፀሙት ወንጀል የጥፋተኝነት ፍርድ መተላለፉ የሚታወስ ነው።

በዚህም መሰረት በዛሬው እለት ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤት በተከሳሾች የዋስትና መብታቸውን በተመለከተ የተሰጠውን ውሳኔ የስር ፍርድ ቤቱ የሻረባቸው ተከሳሾች የክስ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

Federal Attorney general

Exit mobile version