Site icon ETHIO12.COM

ትህነግን ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ማድረግ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለምፍታት እንደማይጠቅም ለኖርዌይ ልዑክ ገለጻ ተሰጠ

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ይህን የተናገሩት በኖርዌይ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ህንሪክ ቱን የተመራውን ልዑክ ባነጋገሩበት ወቅት ነው። የአሸባሪው ህወሓት ቡድንን ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ማድረግ ግጭቱን በሠላም ለመፍታት አያስችልም ሲሉ አስታወቁ። በሁለትዮሽና በኢትዮጵየ ወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ በማተኮር ተወያይተዋል።

በወቅቱም አምባሳደር ሬድዋን በኢትየጵያ እና በኖርዌይ መካከል ለረጅም ዘመን የዘለቀውን ዲፕሎማሶያ ግንኙነት አንስተው፣ ኖርዌይ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት እና የሀገራዊ የሪፎርም ስራዎችን በመደገፏ ምስጋና አቅርበዋል።

አምባሳደር ሬድዋን የህወሃት ቡድንን ተፈጥሯዊ ባህሪይ እና ግጭቱ የተካሄደበት ተጨባጭ ሁኔታ በመገንዘብ የተደረገ እንቅስቀሴ ቢኖር ኖሮ ግጭቱን በአጭር ጊዜ መቋጨት ይቻል ነበር ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ህወሃት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በእብሪት ግፍ መፈፀሙን እያወቀ የሽብር ቡድኑ የሚያሰራጫቸውን የተጠቂነት ማደናገሪያዎች ሲቀባበል ነበር ብለዋል።

መንግስት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማለም የተለያዩ አዎንታዊ እርምጃዎችን መውሰዱን አምባሳደር ሬድዋን ጠቅሰው፣ የፖለቲካ አመራሮች ከእስር መፈታት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት፣ ሁሉን ቀፍ ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንዲጠናቀቅ በማድረግ ረገድ የወሰዳቸው እርምጃዎች ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።

አክለውም የፌደራሉ መንግስት ለሰላም ካለው ቁርጠኝነት የተነሳም ሰራዊቱ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ ማድረጉን እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲሳለጥ የተቻለውን ጥረት ሁሉ ማድረጉንም አስረድተዋል።

ምንም እንኳ በመንግስት በኩል የተለያዩ አዎንታዊ እርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም የህወሓት የሽብር ቡድን ግን በአፋር በኩል አዲስ ጥቃት በመክፈት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲስተጓጎል አድርጓል ብለዋል።

አያይዘውም ግጭቱ እንዲቆም ከተፈለገ የቡድኑን ጸብ አጫሪነትና የሚፈጽማቸውን የግፍ ተግባራት በማያወላዳ ሁኔታ መኮንን እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቡድኑ የሚፈጽማቸውን የወንጅል ተግባራት በዝምታ ከመመልከት ወጥቶ ተጠያቂ ወደማድረግ የማያመራ ከሆነ ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ የሚደረገውን ጥረት አዳጋች አንደሚያደርገውም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።

ዶ/ር ህንሪክ ዙን በበኩላቸው በኖርዌይ በኩል ለተነሱ ጥያዌዎች ክቡር አምባሳደር ሬድዋን ዝርዝር ማብራሪያ ስለሰጡዋቸው አመስግነው፣ ሀገራቸው በሰሜኑ ግጭትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጉዳዮች እንደሚያሳስባት ገልጸዋል።

በግጭቱ ዙሪያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከወገንተኝነት ያልተላቀቀ፤ ህወሃትን የሚደግፍ አቋም እንደሚያራመን በመንግስት በኩል የሚነሳው ሀሳብ የሚገነዘቡት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመጨረሻም በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን የአፍሪካ ሕብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ኦሊሰንጎን ኦባሳንጆ ለሚያደርጉት ጥረትን በማንሳት ተገቢው ድጋፍ ሊሰጠው እንደሚገባም አንስተዋል።

Via- ENA


Exit mobile version