Site icon ETHIO12.COM

ውድመትና ዘረፋ የደረሰበት የአቡነ ዮሴፍ ተራራ የሕዋ ምርምር ጣቢያን መልሶ ለመገንባት እየተሰራ ነው

በጦርነቱ ውድመትና ዘረፋ የደረሰበትን የአቡነ ዮሴፍ ተራራ የአስትሮኖሚ (የሕዋ ምርምር) ጣቢያ ፕሮጀክትን በአጭር ጊዜ መልሶ በመገንባት ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር በለጠ ሞላ ገልፀዋል።

የሕዋ ምርምር ዘርፍ በአሁኑ ወቅት የሀገር ህልውናን ለማረጋግጥ ትልቅ አቅም ያለው ሀብት ነው ያሉት ዶ/ር በለጠ ጣቢያው ሀገራችን በስፔስና አስትሮኖሚክስ ዘርፍ እውቀት ለማሸጋገርና የስፔስ ቱሪዝምን ለማስፋፋት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የተጠሪ ተቋማት ሥራ አመራሮች ጋር በመሆን በአቡነ ዮሴፍ ተራራ የሚገኘውን የሕዋ አካላት መመልከቻ የምርምር ጣቢያ በጎበኙበት ወቅት ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪና የዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ህብረት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን በላይ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕዋን በጥራት ለመመልከት በቀዳሚነት ተመራጭ ከሆኑ ከፍተኛ ቦታዎች አንዱ ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ሳይንቲፊክ ሱፐርቪዥን ቡድን ክትትል የሚያደርግበትና ከኢትዮጵያም አልፎ በሁሉም ዓለማት ተመራጭ መሆኑ የተገለፀውን ይህን ጣቢያ ለማገዝ ሁሉም አካል እንዲረባረብ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን ከባህር ጠለል በላይ 4,280 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው የምርምር ጣቢያ ፕሮጀክቱ በጦርነቱ ሳቢያ የተመራማሪዎቹ መኖሪያ ቤቶች፣ የሳተላይት መረጃ መቀበያ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት መስጫና የሕዋ አካላት መመልከቻ መሳሪያዎቹ ዘረፋና ውድመት ተፈጽሞባቸዋል።

EBC Report

Exit mobile version