Site icon ETHIO12.COM

“ወልቃይት የአማራ ሕዝብ የትግል አስኳል ነው” ይልቃል ከፋለ

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ወጣቶች ከአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ጋር እየመከሩ ነው።

በምክክር መድረኩ ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ(ዶ.ር) ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ጌታቸው ጀምበር (ዶ.ር)፣ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው፣ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ወጣቶች ተገኝተዋል።

ወጣቶቹ በተዘዋወሩበት አካባቢ አማራዊ አንድነትን አጠንክረው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ኃላፊ ጋሻው ተቀባ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ነፃነቱን በልጆቹ መስዋእትነቱን ማረጋገጡን ነው የተናገረው። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ወደ ቀደመ ማንነቱ እንዲመለስ ከፍተኛ ትግል ሲያደርግ እንደነበርም ገልጿል።

የወልቃይት ጠገዴ ትግል በመላው አማራ እንደነበርም አስታውሷል።

የጉብኝቱ ዓላማ የወልቃይት ጠገዴ ወጣቶች ባሕላቸውንና እሴታቸውን ለሌሎች የአማራ አካባቢዎች እንዲያጋሩና እነርሱም የሌሎች አካባቢዎችንም እንዲያውቁ መኾኑንም አንስቷል። ጉብኝቱ በተሳካ መንገድ መካሄዱንም ገልጿል።

የአማራ ክልል መንግሥት ወጣቶቹ ከወንድሞቻቸው የአማራ ክልል ወጣቶች ጋር ግንኙነት እንዲያደርጉ ስላደረገ ምሥጋና አቅርቧል።

በምክክር መድረኩ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የክልላችሁን አካባቢ በስኬት ጎብኝታችሁ በመገናኘታችን እንኳን ደስ ያለን ብለዋል። ሸፍታውና ዘረኛው የትህነግ ቡድን የአማራን ማኅበረሰብ ከአማራ ለመለየትና ከራሱ ጋር ለማቀላቀል የፈፀመው ወንጀል ታሪክ የማይረሳው ነውም ብለዋል። ሕዝቡ ከዓመታት በፊት ጀምሮ ከፍተኛ ትግል አድርጓልም ነው ያሉት። አሸባሪው ቡድን ግን ጥያቄ የሚያነሱትን በመግደልና በማሰር ዘግናኝ ድርጊት ፈፅሟልም ነው ያሉት።

የአማራ ሕዝብ ኹሉንም በሰላም ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ እንደነበር የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ ግፉ ሞልቶ ሲፈስስ ግን የአማራ ሕዝብ መነሳቱንም ተናግረዋል ። የአማራ ሕዝብ የነፃነት ትግል የለኮሰው ጀግናው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ምሥጋናና አድናቆት ይገባዋልም ነው ያሉት። የወልቃይት ጠገዴ ትግል የማንነት መለኪያ ተደርጎ የሚወሰድ፣ የአማራን ትግል ቅርፅ ያስያዘ መኾኑንም ተናግረዋል። የአማራ ሕዝብ ለማንነቱ የሚሞት መኾኑን በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት።

ትግሉ የሚቀጥል እንደሚኾንም አንስተዋል። ወራሪው ቡድን የአማራን ሕዝብ ለማጥቃት የሚንቀሳቀሰው የወልቃይት ጠገዴን ጥያቄ ለማፈን እንደኾነም ተናግረዋል። የአማራ ሕዝብ የመጀመሪያ የሚባለውን ድል ወያኔን በመደምሰስ አካባቢው ነፃ ኾኗልም ነው ያሉት። ድሉ እንዲመጣ ላደረጉት የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ምሥጋና ይገባቸዋልም ነው ያሉት።

ወልቃይት የአማራ ሕዝብ የትግል አስኳል ነው ብለዋል።

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ብዙ ችግር እንዳለ የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ መንግሥት መፍትሔ ለመስጠት የሚችለውን ኹሉ እያደረገ መኾኑንም ገልፀዋል። ለዞኑ እየተደረገው ያለው ድጋፍ በቂ አለመኾኑንም አንስተዋል። በቂ ያልሆነው በፌዴራል መንግሥት በጀት ባለመመደቡ መኾኑንም ተናግረዋል።

ወጣቶቹ በዓላማ ፀንተው እንዲታገሉም አሳስበዋል። ትግሉ እስኪቋጭ ድረስ በፅናት መታገል ይገባልም ነው ያሉት።

አማራ በበርካታ አካባቢ የተጎዳ መኾኑንም አንስተዋል። የወልቃይት ጠገዴ የመሠረተ ልማት ችግር አግባብ ባለው መንገድ እንዲፈታ እንደሚሠሩም አስታውቀዋል።

ወቅቱ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከአማራ ወገኑ ጋር በሰላም የሚኖርበት ነውም ብለዋል። ወልቃይት እንኳን ለራሱ ለሌሎች አካባቢዎች የሚተርፍ እምቅ አቅም ያለው መኾኑን ነው ያነሱት። ወልቃይትን የልማት ምድር እናደርገዋለንም ነው ያሉት። የክልሉ መንግሥት በወልቃይት የመንግሥት መዋቅር እንዲጠናከር እና ሕጋዊ እልባት እንዲያገኝ ይሠራልም ነው ያሉት።

“የክልላችሁን አካባቢ እንዳያችሁ ኹሉ ሌሎች ወጣቶችም ወልቃይትን እንዲጎበኙ እናደርጋለንም” ብለዋል።

አንድነታችን ከተጠናከረ ሊለያየን የሚችል አንድም ኃይል የለም ነው ያሉት። “ተደራጁ የክልሉ መንግሥት ያግዛል” ብለዋቸዋል። በጥቃቅን ችግር እንዳትበገሩ ሲሉም አደራ ብለዋቸዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ – ባሕር ዳር: የካቲት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ)

Exit mobile version