Site icon ETHIO12.COM

ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል የተሰጠ መግለጫ!!

የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ኩራት የሆነው የአድዋ ድል በዓል በሀገራችን የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ለ126ኛ ጊዜ “ዓድዋ ለኢትዮጵያዊያን ህብረት ለአፍሪካ የነፃነት ጮራ” በሚል መሪ ቃል በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር ይከበራል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል እንኳን ለ126ኛ ጊዜ ለሚከበረው የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ኩራት ለሆነው የአድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ የሚል መልዕክት ያስተላልፋል፡፡

ጥንት ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን በአንድነት ተባብረው የኢትዮጵያን ነፃነት በጀግንነት ጠብቀው ለአሁኑ ትውልድ እስከ ሙሉ ክብሯ አስረክበዋል። የአሁኑ ትውልድም ከአባቶች እና እናቶች የተረከበውን አደራ ጠብቆ ሉዓላዊነትና ክብሯን እስካሁን ድረስ አስከብሮ ይገኛል፡፡

ለዚህም ጉልህ ማሳያ ወራሪውና አሸባሪው የህወሃት ጁንታ ቡድን ሀገር ለማፍረስ የከፈተብንን ጥቃት በማክሸፍና እስከ ህይወት መስዋትነት ጭምር በመክፈል የህግ የበላይነትን አስከብሮ ታላቅ ገድል ማስመዝገቡ ነው፡፡

በተጨማሪ ትውልዱ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች በመጠበቅ የግድቡ ግንባታ ለአፍታም ሳይቆረጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረስ አስችሏል፡፡

ዘንድሮ የሚከበረው የአድዋ ድል በዓልን ልዩ የሚያደርገው እነዚህን ታላላቅ ድሎች በተጎናፀፍንበት ማግስት መከበሩ ነው፡፡

በመሆኑም የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ኩራት የሆነው የአድዋ ድል በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ከፍተኛ ዝግጅት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ በዓሉ በሰላም እንዳይከበር አንዳንድ የግል ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የበዓሉን ድባብ የሚያበላሽ ድርጊት ለመፈፀም እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ የጋራ ግብረ-ሃይሉ ደርሶበታል፡፡

ስለሆነም እነዚህ ፀረ ሰላም ኃይሎች ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ እያሳሰበ የማይታቀቡ ከሆነ ግን ግብረ-ኃይሉ አስፈላጊውን ጥብቅ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ያስታውቃል፡፡

በመጨረሻም መላው ህዝባችን ይህንን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በፍጥነት ለጋራ ግብረ-ኃይሉ ጥቆማ በስልክ ቁጥር 251115-52-63-03፣ 251115-52-40-77፣ 251115-54-36-78 እና 251115-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች እንዲጠቀምና በአካባቢው ላለ የፀጥታ ኃይል መረጃውን በአካል ማድረስ እንደሚችል አስታውቋል፡፡

የካቲት 22 ቀን 2014 ዓ.ም

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል

አዲስ አበባ

Exit mobile version