Site icon ETHIO12.COM

ለትህነግ ሊተላለፍ እንደነበር የተጠረጠረ ከሶስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር በላይ ተያዘ

ለአሸባሪው ትህነግ ሊተላለፍ እንደነበር የተጠረጠረ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ በአፋር ክልል ሎግያ ከተማ መያዙን የሠመራ-ሎግያ ከተማ አስተዳደር ፓሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያ ኃላፊው ኮማንደር ቢልኢ አህመድ ዛሬ እንደገለጹት ብሩ የተያዘው ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ በሆቴሎች በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻና የቁጥጥር ስራ ነው።

ሎግያ የሀገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ መስመር የሚያቋርጠው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተጠናከረ መደበኛ የወንጀል መከላከል ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

ኃላፊው እንዳሉት ከዚህም በተጓዳኝ የሽብር ቡድኑ የጥፋት ተላላኪዎችን ለመመከት እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ የሚደርስ ጥብቅ የፀጥታና ቁጥጥር ስራ በየአካባቢው እየተከናወነ ነው።

ለሽብር ቡድኑ ተላላኪዎች እንቅስቃሴ ምቹ ሊሆኑ የሚችሉ መውጫና መግቢያ ቦታዎችን በመለየት ህብረተሰቡን ያሳተፈ ጥብቅ የቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በተጠቀሱት ቀናት በተካሄደው የቁጥጥር ስራ በሎግያ ከተማ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ ሆቴሎች ውስጥ ተደብቆ ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቀዋል።

በሎግያ ከተማ የካቲት 18 ቀን 2014 ዓ.ም ምሽት አራት ሰዓት ላይ ፖሊስ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ አራት ተጠርጣሪዎች አልጋ በያዙበት ሆቴል 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር እንደያዙ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም በተመሳሳይ ሰዓት ስድስት ተጠርጣሪዎች አልጋ በያዙበት ክፍል ከ1 ሚሊዮን 650 ሺህ ብር ደብቀው መገኘታቸውን ኮማንደር ቢልኢ አስታውቀዋል።

በሆቴሎቹ በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻና ጥብቅ የቁጥጥር ስራ ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ ያሳያል።

ተጠርጣሪዎቹ ኪልባቲ-ረሱ ተፈናቅለው የመጡ ነጋዴዎች መሆናቸውን ቢገልጹም፤ የተያዘው ገንዘብ የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎችን በመጠቀም ለሽብር ዓላማው ማስፈጸሚያ ሊውል እንደሚችል የሚያመለክቱ አጠራጣሪ ነገሮች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በየአካባቢው የሚመለከታቸውን ፀጉረ ለውጥና አጠራጣሪ የግለሰቦች እንቅስቃሴ ፈጥኖ ለፓሊስ በማሳወቅ ለራሱና ለከተማው ሰላም መጠበቅ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮማንደር ቢልኢ አሳስበዋል።

(ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version