Site icon ETHIO12.COM

በእነ ታደሰ ወረደ የክስ መዝገብ ስር የተከሰሱ የህውሐት ወታደራዊ አመራሮች የክስ መቃወሚያ በጽሁፍ ለችሎቱ አቅርበዋል

በእነ ጄነራል ታደሰ ወረደ እና ሌ/ጀነራል ጻድቃን ገ/ተንሳይ የክስ መዝገብ ስር የተከሰሱ የህውሐት ወታደራዊ ቡድን አመራሮችና አባላት በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ ባለ 43 ገፅ የክስ መቃወሚያ በጽሁፍ ለችሎቱ አቅርበዋል።

ክስ ከቀረበባቸው 74 ተከሳሾች ውስጥ ጀነራል ታደሰ ወረደና ሌ/ጀ ጻድቃን ገ/ተንሳይን ጨምሮ ከ1ኛ እሰከ 47ኛ ፣ 49ኛ፣50ኛ እና ከ52ኛ እስከ 56ኛ ያሉ በአጠቃላይ 54 ተከሳሾችን ፖሊስ ማቅረብ ባለመቻሉ የጋዜጣ ጥሪ መደረጉን ተከትሎ ተከሳሾች ሳይቀርቡ በመቅረታቸው ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል ፍርድ ቤቱ የክስ ሂደቱ ተከሳሾቹ በሌሉበት እንዲታይ በመወሰን የተከሳሾችን ክስ ለመስማት ለየካቲት 22/2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱ ይታወቃል፡፡

በዚህም መሰረት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዛሬ የቀረቡት ኮ/ል ገ/መስቀል ገ/ኪዳን ፣ ኮ/ል ዶ/ር አለም ብረሃንን ጨምሮ 20 ተከሳሾች መሆናቸውን አረጋግጧል።

ቀጥሎም የዐቃቤ ሕግ ክስ ተነቧል፡፡ የተከሳሾች ጠበቆችም ባለ 26 ገፅ የክስ መቃወሚያና ባለ 17 ገፅ የህገ-መንግስታዊ ትርጉም ጥያቄዎችን በአጠቃላይ ባለ 43 ገፅ መቃወሚያ በጽሁፍ ለችሎቱ አቅርበዋል።

ፍርድ ቤቱም በመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ላይ የዐቃቤ ህግ ምላሽ ውጤት ለመጠባበቅ ለመጋቢት 23/2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተከሳሾቹ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1) (ሀ)(ለ)እና አንቀጽ 33፣35፣38 እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁ 1176/2012 አንቀጽ 3/2 ድንጋጌን በመተላለፍ ፤ በሃገር ደረጃ ከሚያዝያ 2010 ዓ.ም ጀምሮ በነበረው የአመራር ለውጥ ምክንያት ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ( ሕ.ወ.ሓ.ት) ድርጅት በፌደራል መንግት ያለንን ስልጣን በሃይል ተገፍተን እንድንለቅ ተደርጎ የትግል መስመራችን ተቀባይነት አጥቶ የትግራይን ህዘብ ለማዳከምና እኛንም ለማጥፋት የፌደራል መንግስቱ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ በአመፅ የፌደራል ምንግስቱን ከስልጣን ማስወገድና ስልጣኑን መቆጣጠር ያስፈልጋል በሚልና ይሄን ደግሞ ተግባራዊ ለማድረግ በቁጥር 6 /ስድስት / መሰረታዊ ስትራቴጂ ማዕከሎችን የኢኮኖሚ ፣የማህበራዊ ጉዳይ ፣የውጭ ግንኙነት ፣የፖለቲካ ፣የፕሮፓጋንዳና የፀጥታ ክላስተር ኮሚቴዎችን በማደራጀትና በማቋቋም በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ጥቅምት 24/2013 ጀምሮ የህውሐት የሽብር ቡድንን ተልኮ በመቀበል ወታደራዊ ቡድን በማቋቋምና በመምራት በመከላከያ ሰራዊት፣ በፌደራል ፖሊስ በአማራና በአፋር ክልሎች እንዲሁም በኤርትራ ላይ በትጥቅ የታገዘ ጥቃት ማድረስ ወንጀል የፖለቲካዊ አላማ ለማራመድ በማሰብ በልዩ ወንጀል በህብረትና በማደም ተካፋይ መሆናቸው በክሱ ንባብ ላይ ተገልጧል።

Exit mobile version