Site icon ETHIO12.COM

“አትንኩኝ ባይ እለኸኞች፣ የበረሃ መብረቆች”

በእናት ሀገር ከቃል እልፍ ከአቋም ዝንፍ የለም። ሀገር ከተጣራች፣ ለሠንደቅ ተነሱ ካለች ችሎ ከቤቱ የሚያድር፣ ከጦር ግንባር የሚቀር አይገኝም። ኢትዮጵያ ይሏት ምድር፣ ኢትዮጵያዊነት ይሉት ምስጢር፣ የማይመረመር፣ ለምንም የማይበገር፣ በአሸናፊነት ብቻ የሚኖር ረቂቅ ነው።

ስሟን ጠርቶ የተነሳ ኹሉ በድል ይመለሳል። ኢትዮጵያን ብሎ የዘመተ ጠላትን በአሻገር ይመልሳል። በጠላት ቀዬ በኩራት ይነግሣል፣ በአሸናፊነት ይመላለሳል። የጀግኖች ምድር፣ የኃያሎች ሀገር፣ በድል የፀናች፣ በጀግና ልጆቿ የተጠበቀች፣ በኃያል ክንዶች የተከበበች ኃያል።

ጠላቶች በየዘመናቱ ሊደፍሯት ይነሳሉ፣ ተመትተው አንገት ደፍተው ይመለሳሉ፣ የኢትዮጵውያንን ክንድ ይቀምሳሉ። እርሷም የሚመጡትን ለመምታት ፣ የገጠሟትን ለመርታት ታድላለችና የመጡትን ኹሉ ታሸንፋለች።

ወርኃ የካቲት፥ የኢትዮጵያ ስም ከታሪክ ጫፍ ከፍ ያለበት፣ በማይለቅ ቀለም፣ በማያረጅ ብርና የተፃፈበት፣ የነጭ አንገትና ቅስም የተሰበረበት፣ የቀኝ ግዛት አራማጆች የደነገጡበት፣ የነጭ ሠራዊት በጥቁር ምድር፣ በጥቁር ክንድ ያለቀበት፣ የሮም አደባባዮች የጨለሙበት፣ የኢትዮጵያ ጎዳናዎች በድል የናኙበት፣ አፍሪካውያን የብርሃን ጮራ ያዩበት፣ ከጨለማ የተላቀቁበት፣ የነፃነት መንገድ ያዩበት የዓድዋ የድል በዓል በኢትዮጵያ ምድር ተከብሯል። የዓድዋ የድል በዓል በተከበረበት ወር ታዲያ ሌላ ወራሪ መጥቶ ሀገር ወርሮ ነበር። ኢትዮጵያውያን ጀግኖችም ተጋድሎ ላይ ነበሩ።

በረሃው በሚናደፈው፣ ሙቀቱ በሚጋረፈው በምሥራቅ ኢትዮጵያ ከበረሃው የረቀቀ፣ ከሙቀቱ የረቀቀ ውጊያ ይደረግ ነበር። ኢትዮጵያውያን የዓድዋ ድል በሚከበርበት በዚያ ታላቅ ወር ሌላ የድል ቀን ለመጨመር ትንቅንቅ ላይ ናቸው። ለዚያች ምስጢራዊት ሠንደቅ፣ ለዚያች ረቂቅ ምድር ላባቸውን፣ ደማቸውን፣ አጥንታቸውንና ሕይወታቸውን እየሰጡ ነው።

የተከበረችውን፣ በአጥንትና በደም የፀናችውን ሀገር በእኛ ዘመን ማንም አይደፍራትም፣ ጠላት አይወራትም፣ ክፉ ሰው አይነካካትም ሲሉ በዚያ ነዳድ በረሃ በበዛበት ምድር አያሌ ጀብዱዎችን እየፈፀሙ ነው። አስደማሚ ገድሎችን እየተጋደሉ ነው፣ አስገራሚ ውጊያ እያደረጉ ነው።

ሰሜንና ደቡብ ሶማሊያ ተብለው በኹለት ቀኝ ገዢ ሀገራት ሲተዳደሩ የነበሩት አንድ የሚኾኑበት ዘመን መጣ። አፍሪካውያን ከቀኝ ገዢዎች ነፃ እየወጡ ነበርና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሶማሊያ መንግሥት እንዲመሠረት ወሰነ። በ1952 በሶማሊያ መንግሥት ተመሠረተ።

የሶማሊያ መንግሥት በምሥራቅ አፍሪካ ታላቋን ሶማሊያ ለመፍጠር የኢትዮጵያን ምድር ኦጋዴንን መያዝ ከዕቅዱ አንደኛው ነበር። አዲስ የተመሠረተው የሶማሊያ መንግሥትም በ1953 በኢትዮጵያ ትንኮሳ ፈፀመ። የኢትዮጵያ ልበ ብርቱ ጦርም ረጋግጦ አባረረው። ለዓመታት ራሱን አደራጅቶ በ1956 በፌርፌር በኩል ዳግም ወረራ ከፈተ። አሁንም ክንደ ብርቱው የኢትዮጵያ ጦር ድምጥማጡን አጠፋው።

ኢትዮጵያን መንካት ከኢትዮጵያ ምድርም ቆርሶ መውሰድ እንደማይቻል የተረዳው የሶማሊያ መንግሥት በሽንፈቱ እየቆዘመ ለዓመታት ተቀመጠ። አዲስ ወረራ ግን ማሰቡ አልቀረም።

ፕሬዝደንት አብዲራሺድ አሊ ሸርማርኬን በመንፈቅለ መንግሥት አስወግዶ ሥልጣን የጨበጠው የዚያድ ባሬ መንግሥት ድንበር ማስፋፋትና ታላቋን ሶማሊያን ለመገንባት ተንቀሳቀሰ። ከአረብ ሀገራት በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ግዙፍ የምድር ጦር፣ የዓየር ኃይልና የባሕር ኃይል ገነባ። በዘመናዊ መድፎች፣ ታንኮች፣ ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች፣ በፈጣን ተዋጊ ሚግ አውሮፕላኖች፣ በአየር መቃወሚያ መሳሪያዎች፣ በፀረ ሰውና በፀረ ታንክ መሣሪያዎች፣ ረጅም ርቀት በሚመቱ መትረጌሶችና በሌሎች ሠራዊቱን አስታጠቀ።

የሶማሊያ መንግሥት እንዲህ እየተደራጀ በነበረበት በዚያ ዘመን በኢትዮጵያ ዘውዳዊ ሥርዓት እክል ገጥሞት በወታደራዊ መንግሥት ተገልብጧል። ለረጅም ዘመናት በነገሥታት ስትተዳደር የነበረችው ኢትዮጵያ የንጉሡን ሥርዓት ሽሮ አዲስ ሥርዓት የያዘ መንግሥት ያስተዳድራት ጀምሯል። ወታደራዊ መንግሥቱ ሀገሪቱን ተቆጣጠረ። በኢትዮጵያ የተነሳውን ለውጥ ያየው የሶማሊያ መንግሥት ደስታው ከፍ አለ።

ያልጠና መንግሥት ያላትን ሀገር መወረር ቀላል መስሎ ታየው፣ የሶማሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ነፃ አውጭ ነን ባይ ቡድኖች ጋር ወዳጅነት መፍጠር ዋነኛ ዕቅዱ አድርጎ ተነሳ። በዚያ መሠረትም ኢትዮጵያን በአራቱም አቅጣጫ በጦርነት ማዋከብ ነበር ዓላማው።

የሶማሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚያግዙትን ቡድኖች ካደራጀ በኋላ የወረራ ተግባሩን መፈፀም ጀመረ። በደሎችንም በኢትዮጵያውያን ላይ ይፈፅም ጀመር። በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ድርጅቶችም በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፈቱ። አዲሱ መንግሥት ከባድ ፈተና ገጠመው። የዚያድ ባሬ ጦር ደጋሃቡር፣ ቀብሪደሃር፣ ዋርዴር፣ ጎዴና እና ሌሎችን የምሥራቅ ኢትዮጵያ ከተሞችን ወረረ።

የኢትዮጵያ ሠራዊት በውስጡ ወረራውን የሚደግፉ ሠዎች ነበሩበት እና ረግቶ እንዳይዋጋ እክል ገጠመው። ይህን ያዩት ደፋሩ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጦር ይዘው ወደ ካራማራ ገሰገሱ። መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም አዲሱ መንግሥት በቂ ጦር አሰልጥኖ እና አደራጅቶ ሀገር የወረረውን የሶማሊያን ጦር ረግጦ እስኪያባረር ድረስ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዲከላከል ትእዛዝ ሰጡ። በውስጡ ተሰግስገው ጦሩን ሲያሸብሩ የነበሩት በጦሩ ፊት ተቀጡ። የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዕዛዝ ሀገርን ከአደጋ የታደገ እንደነበር ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ጽፈዋል።

ኢትዮጵያ በወራሪዎች እና በባንዳዎች ክፉ ሥራ ተወጠረች። አዲሱ መንግሥት በየአቅጣጫው ተወጠረ። ከሀገር መሬት አንድ ኢንች አይወሰደም የሚሉት ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አዲስ ስልት ቀየሱ። በሥራ ተጠምደው በርካታ ተግባራትን ፈፀሙ። ሀገራቸውን የወረረውን ወራሪ ለማስቆም የእናት ሀገር ጥሪ ማድረግ ግድ አላቸው።

መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በሚያዚያ 4/1969 ዓ.ም በመገናኛ ብዙኃን ፊት ቀርበው ሀገራዊ ጥሪ አቀረቡ። “ታፍራና ተከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ ተደፍራለች። በአሁኑ ሰዓት የአቢዮታዊት እናት ሀገራችን ዳር ድንበርና የማይገሰሰው አንድነታችን በውጭ ኃይል እየተደፈረ ነው። በአብዮታችን እና በአንድነታችን በጠቅላላው በብሔራዊ ኅልውናችን ላይ የሚደረገው ወረራና ድፍረት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሷል። ለብዙ ሺህ ዘመናት አክብሮን የኖረው አኩሪ ታሪካችን በዚህ አብዮታዊ አዲስ ትውልድ መጉደፍ የለበትም። ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ክብርህን እና ነፃነትክን ለመድፈር ሀገርህን ለመቁረስ የመጣውን ወራሪ ለመደምሰስ የምትዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው። ተነስ ! ታጠቅ ! ተዋጋ ! እናሸንፋለን !! ” ሲሉ መረር ያለ ሀገራዊ ጥሪ አቀረቡ።

ሀገር ጠርታው ተኝቶ የማያድረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር ዳር ተሰማማ። የተከበረች ሀገሩን የደፈረውን ጠላቱን ለመደምሰስ ተንቀሳሰ። ንቡ ተነሳ። አንበሳው አገሳ። ወዮለት ለዚያ ወራሪ። ኢትዮጵያውያን ወደ ጦር ማሰልጠኛ ተመሙ። የእናት ሀገር ፍቅር ሰንቀው ሰለጠኑ። ጠላት ወረራውን እያሰፋ ነው።

የሶማሊያ መንግሥት ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ለማግኘት ሶሻሊስት ነኝ ሲል ከሶቪየት ኅብረት ጋር ተወዳጀ። ሕንድ ውቅያኖስን ለመቆጣጠር የሰፋ ፍላጎት ያላት ሶቪየት ኅብረት ከሶማሊያ ጋር ተወዳጀች። የሶማሊያን ጦርም አስታጠቀች። በወቅቱ የኢትዮጵያ ወዳጅ የነበረችው አሜሪካ የኢትዮጵያ ሠራዊትን በመሳሪያ ለማገዝ አልፈለገችም። የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ቢጠይቃትም ፈቃደኛ አልነበረችም። ይባስ ብላ ኢትዮጵያ ክፍያ የፈፀመችባቸውን መሣሪያዎች ላይ እገዳ ጣለች።

ኢትዮጵያ በካፒታሊዝም እና በሶሻሊዝም ከተከፈለው ዓለም ወደ አንደኛው ሳትኾን ቀረች። ይህን ያየው ወታደራዊ መንግሥት ወደ ሶሻሊዝም ማምራት እንዳለበት ወሰነ። ከሶሻሊዝም ጋርም ግንኙነት ፈጠረ። ሶቪየት ኅብረትም ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ሶሻሊዝምን እንዲገነቡ ሐሳብ አቀረበች። ሶማሊያ ግን አሻፈረኝ አለች። ቀስ በቀስ ሶማሊያ እና ሶቪየት ኅብረት ተቃረኑ። ይህ ጉዳይ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ ነበር።

መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በሶቪየት ኅብረት ጉብኝት አደረጉ። ከፕሬዝዳንት ብሬዤኔቭ ጋርም ተወያዩ። ውይይቱም ፍሬ አፈራ። በሌሎች ሀገራትም ጉብኝት አደረጉ። ድጋፍም አገኙ። ኩባም ከፍተኛ እገዛ አደረገች።

የማይቀረውና የቀለጠው ጦርነት ተጀመረ። ኢትዮጵያውያን ሠንደቃቸውን አስቀድመው በዚያ በረሃ ከጠላት ጋር ተናነቁ። በወራሪው ኃይል የተያዙ አካባቢዎችን ነፃ እያወጡ ጠላትን እንደ ቅጠል እያረገፉ ቀጠሉ። የዚያድ ባሬ ጦር የኢትዮጵያን ጦር መቋቋም ተስኖት በበረሃ ወድቆ ቀረ። ብዙው ተማረከ። ነብስ አውጭኝ ያለው ፈረጠጠ። ዚያድ ባሬ አብዝቶ ደነገጠ። የተኩራራበት መንግሥት አደጋ ገጠመው።

ወደ ካራማራም ገሰገሰ። በየካቲት 23 የዓድዋ የድል በዓልን ያከበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሌላ ድል እየቀረበለት ነው። በእልህ እና በሀገር ፍቅር የተመላው የኢትዮጵያ ሠራዊት ካራማራን በጦር አጠረው። የኢትዮጵያ ጦር በሰማይ በምድር ጠላትን ይደበድበው ጀመር። አትንኩኝ ባይ ጀግኖቹ፣ የበረሃ መብረቆቹ ከበረሃው የበለጠ ንዳድ ክንዳቸውን በሶማሊያ ወራሪ ኃይል ላይ አሳረፉ። የሶማሊያ ጦር ተቀለብልቦ ገብቶ ድባቅ ተመታ።

በምሥራቅ በካራማራ የኢትዮጵያ የድል መብራት ከፍ ብሎ በራ። ጠላት ድምጥማጡ ወጣ። ካራማራ ተራራ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ተመላች። በደስታ ዘለለች። ምስጢራዊት አረንጓዴ ቢጫ ቀይዋ ሠንደቅ በድል ተውለበለበች። የማይቀረው ድል ለእርሷ ብቻ የተሰጠ የሚመስለው አሸናፊነት ለኢትዮጵያ ኾነ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በየካቲት 23 የዓድዋ ድልን አክብሮ በየካቲት 26 አዲስ ድል ተቀዳጀ። ሌላ የድል በዓል ለትውልድ አስቀመጠ።

ዚያድ ባሬ ከሽንፈቱ በኋላ ተቀባይነቱ እየሟሸሸ መጣ። የኢትዮጵያ ጀግኖች ኃያልነታቸውን ያሳዩበት፣ ደማቸውን ያፈሰሱበት፣ አጥንታቸውን የከሰከሱበት፣ ሕይወታቸውን የገበሩበት ጦርነት በኢትዮጵያ የበላይነት በካራማራ ተጠናቀቀ።

መቅደስ ዐቢይ የካራማራ ግራሮች በሚለው መጽሐፏ ” ድል ለትልቋና ለጥንታዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ ከተፈቀዱላት በረከቶች አንዱ ነገር ነው” ብለዋል። ድልን የታደለች ኢትዮጵያ ዛሬም በድል ነገም በድል ትገሰግሳለች። ለድል ተፈጥራለችና። ክብር ከራስ በፊት ሀገርን ላስቀደሙት፣ በደማቸው ሀገር ላፀኑት፣ በአጥንታቸው ሀገር ላቆሙት፣ ለሕይወታቸው ላልሳሱት።

በታርቆ ክንዴ – (አሚኮ)

Exit mobile version