Site icon ETHIO12.COM

ለአፍሪካ የጋራ መገበያያ ገንዘብ መመሥረት ደቡብ አፍሪካ ሙሉ ድጋፏን እንደምትሰጥ አስታወቀች

ለአፍሪካ አኅጉራዊ የንግድ ግብይት ለሚያገለግለው የጋራ መገበያያ ገንዘብ መመሥረት ደቡብ አፍሪካ ሙሉ ድጋፏን እንደምትሰጥ አስታውቃለች።

የደቡብ አፍሪካ የዓለም ዐቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ናሊዲ ፓንዶር የአፍሪካ ማዕከላዊና ኢንቨስትመንት ባንኮች እንዲሁም የአፍሪካ የገንዘብ ድርጅት መቋቋም አንዱ ምክንያት የአኅጉሪቷን ንግድ በአንድ የመገበያያ ገንዘብ ለማሳለጥ ነው ብለዋል።

የመገበያያ ገንዘቡ መመስረት እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ በመሆኑ ይህንን ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ደቡብ አፍሪካም በ1991ዱ የአቡጃ ስምምነት መሰረት የአፍሪካን የንግድ፣ የአገልግሎትና የካፒታል ዝውውሮችን የሚያሳልጡ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ናት በማለት አስታውቀዋል።

በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባዎች ላይ ለጋራ መገበያያው ፈጥኖ እውን መሆን የተለያዩ ሥራዎችን እንደምትሰራ ነው ያስታወቁት።

የአፍሪካ የገንዘብ ተቋማቱ ለጋራ መገበያያው ወደ ሥራ መግባት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ያሰመሩበት ሚኒስትሯ እነዚህ ተቋማት የአጀንዳ 2063 ፕሮጀክት አካል ናቸው ማለታቸውን ኒውስ 24ን ዋቢ አድርጎ ኢዜአ አስነብቧል።

Exit mobile version