የ150 ቢሊዮን ዩሮ የአፍሪካ-አውሮፓ የኢንቨስትመንት እቅድ ይፋ ሆነ

በቤልጄም ብራሰልስ ሲካሄድ የቆየው 6ኛው የአፍሪካና የአውሮፓ ህብረቶች የመሪዎች የጋራ ጉባኤ መጠናቀቁን ተከትሎ ስምምነት በደረሱባቸው ጉዳዮች ላይ የጉባኤውን የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

ስምንት ነጥቦችን ባካተተው የጥምር ጉባኤው መግለጫ የአፍሪካና የአውሮፓ ህብረቶች አጋርነታቸውን ለማደስና በጋራ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ትብብር ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በርካታ ድንገተኛና ተደጋጋሚ ስጋቶች ሁለቱንም አህጉራት የፈተኗቸውን ያህል ተስፋዎችም እንዳሉን ተረድተናል ነው ያሉት በመግለጫቸው።

ለአህጉራቱ አስተማማኝ ደህንነት፣ ሰላም፣ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማትና ብልጽግናን ለማምጣት በጋራ በመስራት የጋራ ራዕያቸውን እንደሚያሳኩም አረጋግጠዋል።

የአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ ህብረት የተዘጋጀውን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደረገውን የ2022 መልዕክት እንደሚደግፈውም ጠቅሷል።

በዓለም አቀፉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ስርጭት ላይ የታየው ኢፍትሐዊነት እንዲስተካከልና ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆንም ሁለቱ ህብረቶች በጋራ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

የአውሮፓ ህብረትም እስከ 2022 አጋማሽ ድረስ 450 ሚሊዮን ዶዝ የኮቪድ ክትባት ለአፍሪካ እንደሚሰጥ በጋራ መግለጫው አረጋግጧል።

425 ሚሊዮን ዩሮ በመመደብም የክትባት ምርትን ማፋጠን፣ ፍትሐዊነትን ማረጋገጥና የባለመያዎች አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት ይሰራል ነው የተባለው።

የአውሮፓ ህብረትም በወረርሽኙ የተዳከመውን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የብድር ስምምነቶችን በመፈተሽ እስከ እዳ ስረዛ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ ማረጋገጡን በመግለጫው ተጠቅሷል።

አጠቃላይ ዓለም አቀፋዊ ፍላጎትን መሰረት በማድረግም አፋጣኝ ገንዘብ ለሚያስፈልጋቸው ሀገራት እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ የሚደረግ ሲሆን ከዚህም አፍሪካ በብዛት ተጠቃሚ ትሆናለች ተብሏል።

በመግለጫው የጋራ እና ዘላቂ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በትንሹ 150 ቢሊዮን ዩሮ የአፍሪካ-አውሮፓ የኢንቨስትመንት እቅድ ይፋ ተደርጓል።

ይህም የትምህርትና የጤና ዘርፍን ያካተተ ሲሆን የአውሮፓ-አፍሪካ የ2030 የጋራ ራዕይን እና አጀንዳ 2063ን ለማሳካት እንደሚያስችልም በመግለጫው ተብራርቷል።

በሁለቱ አህጉራት መካከል ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲኖር የሚሰራ ሲሆን በተለይም የአፍሪካ የነጻ ንግድና ገበያ ስርዓትን እውን ከማድረግ ባሻገርም ነባር የንግድ ስምምነቶችን በመፈተሽ ለቀጣይ የጋራ ስራ የሚሆኑ ትብብሮች ይደረጋሉ ነው ያለው መግለጫው።

የሁለቱ አህጉራት መሪዎች በሰላምና ደህንነት ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከርና ለማደስ መግባባት ላይ የደረሱ ሲሆን የሚያጋጥሟቸውን ስጋቶች በጋራ ለመሻገርም አቅደዋል።

See also  "መከላከያ ሲገፋ የዕርዳታ ካርዶች ተመዘዙ" ሰቆጣ በቁጥጥር ስር ውላለች ! አርብ ገጠመ

የአፍሪካ የስደተኞች ጉዳይ ተቋማትን አቅም በማጠናከር፣ የሀገራትን አቅም በመገንባት፣ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል በማካሄድ የሰዎች ህገወጥ ዝውውርና ስደትን ለመከላከል እንደሚሰሩም አቋም መያዛቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በፀጥታው ምክር ቤትና ሌሎች ዘርፎች ለውጥ ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ ሁለቱም አህጉራት በጋራ ይሰራሉ።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ፣ የመሰረተ ልማት ትስስርን ለማፋጠን፣ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ትብብር ለማሳደግ፣ በሰላምና ደህነነት አብሮ ለመስራት፣ ሁሉም የበኩሉን ርብርብ እንዲያደርግ በመግለጫው ጥሪ ማቅረቡን ኢፕድ ዘግቧል።

Leave a Reply