ETHIO12.COM

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ወይም ሞት እያለ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ የግብርናን ምርት ሰለማሳደግ በስፋት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንን ሪፖርቶች ያሳያሉ። በአፋርና በኦሮሚያ እጅግ ሰፊ የተባለ የበጋ መስኖ ስንዴ መመረቱም ተደጋግሞ እየተወሳ ነው። በአማራ ክልልም በተመሳሳይ ይኸው የበጋ መስኖ እርሻ እንዲበለጽግ የተጀመረው ስራ ፍሬው ማማሩ መልካም ዜና ሆኗል።

በተቃውሞና በማንቋሸሽ መጋኛ የተመታው የአገሪቱ ፖለቲካና ፖለቲከኞች፣ እንዲሁም ምን እንደሚፈልጉና የማንን አጀንዳ እንደሚያራግቡ በግልጽ ባይናገሩም የሚታውቅባቸው ወትዋቾች ይህን የበጋ ስንዴ አዝመራ ሲኮንኑም ማድመጥ ተለምዷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛፍ ሲያስተክሉ፣ ሲተክሉና ስንዴ መካከል ግብተው ከገበሬው ጋር ሲመክሩም በነዚሁ ሃይሎች እየተረገሙ ነው።

ከሰባ እስከ ሰማኒያ በመቶ የሚሆን ለእርሻ ተስማሚ መሬትና በቂ ውሃ ያላት ኢትዮጵያ በምግብ ምርት ራስዋን አለመቻሏና ተረጂ መሆኗ፣ ረሃብተኛ በሚል ህልውናዋ በእርዳታ ስም ሲናጋ፣ በመከረኛ እርዳታ ስም ስትታመስና ጫና ሲደረግባት በተግባር ላዩ ለስንዴ ምርት የተሰጠው ትኩረት አነሰ በሚል እከራከር ሲገባቸው ዳር ሆነው መተቸታቸው እንደ ዜጋ የሚያሳፍራቸውም አሉ።

ከነዚህ መካከል የድብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ በተግባር በሁዋላ ቀር አሰራር እየተጠቀምን እያደገ ያለውን የህዝብ ብዛት መቀለብ አይቻልም በሚል ” ግብርና ወይም ሞት” በሚል የጀመረውን ተግባር ዩኒቨርስቲዎን ጠቅሶ የደብረማርቆስ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዘግቧል። ዩኒቨርስቲው ” ለምን ስንዴ አመረትክ” ተብሎ ነቀፋ እንደሚወርድበት ይጠበቃል። ሙሉ ዘገባውን ከስር ያንብቡ።

የአገራችን የግብርና ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ችግሮችን የመቋቋም አቅም የገነባ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን በመንሸራትት ላይ ያለ ዘርፍ እንደሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጹ ያሳወቀው ዩኒቨርሲቲው ለዘመናት ባልተቀየረ የአስተራረስ ስልት በማደግ ላይ ያለውን የአገሪቱን ሕዝብ ቁጥር የመመገብ ግዴታውን ለመወጣት እየተውተረተረ ያለ ዘርፍ እንደመሆኑ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያስፈልገዋል ብሏል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሰብል ልማትና የግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ የግብርናውን ዘርፍ በምርምር በመደገፍ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡ በያዝነው ዓመትም የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደ አገር ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ማህበረሰቡ የከፋ ረሀብና ችግር ላይ እንዳይወድቅ ለማድረግ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤሊያስ ወረዳ የግዳድ ቀበሌ 255 ሄክታር እንዲሁም በማቻከል ወረዳ ከ48 ሄክታር መሬት በላይ አስፈላጊውን ግባዓትና በማሟላት የበጋ መስኖ ስንዴን እያለማ ይገኛል፡፡

ይህንን የበለጠ ለማሳደግና አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድርግ እየሰራ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ዘመናዊ የግብረና መሳሪያዎችን መግዛቱንም አስታውቋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር እሱባለው መኩ እንደገለፁት አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የግብርና ስራ የሚከናወንበት ስለሆነና አብዛኛውን የሀገሪቱ ምርት የሚመረትበት አካባቢ እንደመሆኑ መጠን የግብራና ስራው ግን ባለመዘመኑ የተነሳ በሚፈለገው መጠን ምርት እየተመረተ አይደለም፡፡

በዚህም የተነሳ ዩኒቨርሲቲው የራሱን ድርሻ ለመወጣት የግብርና መካናይዜሽኑን ሊደግፍ ሚችል አራት የተለያየ የፈረስ ጉልበት ያላቸው የተለያዩ ትራክተሮችና ኮምባይነር በ37 ሚሊየን ብር ግዥ በመፈፀም አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም እርሻ ስራ ተጠቃሚ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው መሳሪያዎቹ ለምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው ብለዋል፡፡

መረጃው የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡

Exit mobile version