Site icon ETHIO12.COM

የፓለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚደረጉ የአሉታዊ መረጃዎች ዘመቻ

በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለያዩ ተቋማት እና ግለሰቦችን ኢላማ ያደረጉ አሉታዊ መረጃዎች በከፍተኛ ደረጃ ይሰራጫሉ። በተለይም ፓለቲካ እና ሀይማኖትን የመሳሰሉ ስሜት ቀስቃሽ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የሚያደረጉ አካላት የአሉታዊ መረጃዎች ዋነኛ ኢላማዎች ናቸው። ይህ ጥናት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማዕከል አድርገው በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚደረጉ የአሉታዊ መረጃ ዘመቻዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና አንድ በክልል ስልጣን ላይ ያለን ፓርቲን እንደ ማሳያ ጥቅም ላይ ውሏል።

ለዚህ ፅሁፍ በአጠቃላይ ከ2011 እስከ 2013 መጨረሻ ባለው ወቅት በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የተሰራጩ 880 አሉታዊ መረጃዎችን ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን እነዚህም አሉታዊ መረጃዎች ከ166 ሺህ በላይ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን በአስተያየት፣ በማጋራት፣ እና በስሜት ምላሽ መልክ ያሳተፉ ናቸው። ከዚህ ውስጥ 56% የአማራ ብልፅግና ፓርቲ፣ 23% አማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ 10% የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ 7% ያህሉ ባልደራስን የተመለከቱ ሲሆን የተቀረው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በጋራ ኢላማ ያደረጉ ናቸው። በተጨማሪም 381 አካውንቶች እነዚህን አሉታዊ መረጃዎችን በመፍጠር እና በማሰራጨት ላይ ተሳትፎ አድረገዋል። ከነዚህ ውስጥ 54% የአማራ ብልፅግናን፣ 34% አብን፤ 19% ኢዜማን፣ 8% ባልደራስን እንዲሁም የተቀሩት አካውንቶች የተለያዩ ፓለቲካ ፓርቲዎችን በጣምራ የአሉታዊ መረጃዎች ኢላማ አድረገው አቅርበዋል።  በአጠቃላይ እነዚህ አካውንቶች ከ22 ሚሊዬን በላይ ለሚሆን ተጠቃሚ ተደራሽ የሆኑ ናቸው።

ለዚህ ጥናት ጥቅም ላይ ከዋሉ 880 አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ 74% የሚሆኑት ሀሰተኛ መረጃዎች፣ 4% የጥላቻ ይዘት ያላቸው መረጃዎች እና 22% ደግሞ ግጭት ቀስቃሽ ይዘት ያላቸው መረጃዎች ናቸው። ከሀሰተኛ መረጃዎች ውስጥ 84% የፈጠራ ይዘት ያላቸው ሲሆን 16% ደግሞ አሳሳች ይዘት ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል። ግጭት ቀስቃሽ ይዘት ካላቸው አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ 64% እነዚህ የፓለቲካ ድርጀቶቹ እና አባላቶቹ ላይ አደጋ እንዲደርስ የሚያነሳሳ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ 30% ተቃውሞን እና ሽብርን የሚቀስቀሱ 5% ደግሞ ግጭት እና የሽብር ጥቃቶችን የሚያሞግሱ እና የሚያወድሱ ናቸው። በተጨማሪም የጥላቻ ይዘት ካላቸው አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ 48% ማንነት ላይ ያተኮሩ ፀያፍ የጥላቻ ስድቦች ፣ 26% ደግሞ የፓለቲካ ፓርቲ አባላነትን መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች ፣ 16% የንቀት እና ማንነትን ዝቅ የሚያደረጉ እና 10% ሰብአዊ ማንነትና ክብርን የሚያዋርዱ ይዘት ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል።

የሀሰተኛ፣ ግጭት ቀስቃሽ እና የጥላቻ ይዘት ካላቸው 880 መረጃዎች ውስጥ 59% የአማራ ብልፅግና ፓርቲን የተመለከቱ ሲሆን የተቀሩት 41% መረጃዎች የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ኢላማ ያደረጉ ከእነዚህ የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ኢላማ ካደረጉ አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ 20% አብንን፣ 10% ኢዜማን፣ 5% ባልደራስን ኢላማ ያደረጉ አሉታዊ መረጃዎች ሲሆኑ 2% ደግሞ እናት ፓርቲ እና ኦፌኮ እንዲሁም የተቀረው 4% መረጃዎች የተለያዩ ፓርቲዎችን በጋራ ኢላማ ያደረጉ መረጃዎችን የያዙ ናቸው።

የአማራ ብልፅግና ፓርቲን ከተመለከቱ አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ 67% ሀሰተኛ መረጃዎች ሲሆኑ 30% ግጭት ቀስቃሽ እንዲሁም የተቀረው 3% መረጃ ደግሞ የጥላቻ ይዘት ያላቸው የማህበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ናቸው። ግጭት ቀስቃሽ ይዘት ካላቸው መረጃዎች ውስጥ 95% የቡድኑ አባላት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ጥሪ የሚያደርጉ እና ብጥብጥ ቀስቃሽ መረጃዎች ሲሆኑ የተቀረው ደግሞ ብጥብጥና ግጭትን የሚያወድሱ መረጃዎችን የያዙ ናቸው።

የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ኢላማ አድርገው ከተሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ 84% ሀሰተኛ መረጃዎች፣ 10% ግጭት ቀስቃሽ እና 6% ያህሉ ደግሞ የጥላቻ ይዘት ያላቸው ልጥፎች ሆነው ተገኝተዋል። ግጭት ቀስቃሽ ይዘት ካላቸው መረጃዎች ውስጥ 87% የድርጀቶቹ አባላት እና ቤተሰቦች ላይ ጉዳት እንዲደርስ የሚቀሰቅሱ እና በአጠቃላይ ብጥበጥን የሚያበረታቱ መረጃዎች ናቸው።

በተጨማሪም የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የተመለከቱ የጥላቻ ይዘት ያላቸው መረጃዎች ሙሉ በሙሉ በፓለቲካ ፓርቲዎች አባላት ማንነትን ማዕከል ያደረጉ የፀያፍ ቃላትን፣የንቀት ቋንቋን የሚጠቀሙ እና ሰብዓዊነትን የሚያሳንሱ የጥላቻ ንግግር አይነቶች ናቸው።  (ምስል 2)

ምስል 1፡ አሉታዊ መረጃዎችን የተመለከተ መረጃ

አሉታዊ መረጃዎቹ ከይዘት አንፃር በዋነኝነት እነዚህን አሉታዊ መረጃዎች የሚያሰራጩ አካላት ያላቸውን አላማ ለማሳካት ወቅታዊ ሁኔታዎችን እየተከተሉ ስሜት ቀስቃሽ ይዘት ያላቸውን አሉታዊ መረጃዎችን በመፍጠር እና በማሰራጨት ላይ ሲሰሩ ይስተዋላል። በተጨማሪም ተመሳሳይ አጀንዳን ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የሚያሰራጩ አካላት በብዛት እንዳሉ መታዘብ ተችሏል። በዚህ ጥናት ላይ ከተስትዋሉ አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ ከመረጃዎቹ ብዛት እና የተሳትፎ ምጣኔ አንፃር በዋነኝነት 6 የፓለቲካ ፓርቲዎችን ኢላማ ያደረጉ ሲሆን እነዚህም አብፓ፣ አብን፣ ኢዜማ፣ እናት ፓርቲ፣ ባልደራስ እና ኦፌኮ (የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ) ሆነው ተገኝተዋል። ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ፓርቲዎችን በጣምራ በማካተት ኢላማ አድርገው የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በብዛት እንዳሉ ለመታዘብ ተችሏል።

የአማራ ብልፅግና ፓርቲን የተመለከቱ አሉታዊ መረጃዎች አብዛኛው ይዘት የሚያጠነጥነው የአማራ ብልፅግና ፓርቲ እና የፌድራል መንግስቱን ከሚመራው የብልፅግና ፓርቲ እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተገናኙ ሴራ ተኮር መረጃዎች ላይ ነው። እነዚህም በዋነኝነት የአማራ ብልፅግና ፓርቲ አባል የሆነበት እና የፌድራል መንግስቱን እየመራ ያለው የብልፅግና ፓርቲ በተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ ለተፈረጀው አነግ ሸኔ የቁስቁስ፣ የገንዘብ እና የሎጅስቲክስ ድጋፎችን እንደሚያደርግ የሚጠቅሱ እና የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ለዚህ ተግባር በማወቅም ይሁን በአቅም ማነስ የተነሳ የተባባሪነትን ሚና ይጫወታል የሚል ይዘት ያላቸው አሉታዊ መረጃዎች ናቸው። ከዚሁ ጋር በተያየዘ የፌድራል መንግስት የአማራ ክልል የተለያዩ አመራሮችን እያስወገደ ነው የሚል እና የፌድራል መንግስት ከህዋሃት ጋር በትብብር በመሆን የአማራ ማህበረሰብ ላይ እስከ ዘር ማጥፋት የደረሰ ጉዳቶች እንዲደርስበት እያደረገ ነው የሚል ይዘት ያላቸው ሀሰተኛ መረጃዎችን ያካትታሉ። በተጨማሪም በአማራ ብልፅግና ፓርቲ አባላት መካከል ውስጣዊ ግጭት ተከስቷል፤ በድርጅቱ እና በኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ መካከል ውዝግብ አለ፤ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ በህቡዕ ለህዋሃት ትብበር ያደርጋል እንዲሁም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ አንድ ክንፍ ነው የሚል ይዘት ያላቸው ልጥፎችን በማህበራዊ ሚዲያው ሲሰራጩ በዚህ ጥናት ላይ ማስተዋል ተችሏል።

ሌላው የአሉታዊ መረጃዎችን የጭብጥ ሀሳብ በአማራ ብልፅግና ፓርቲ እና በሚያስተዳድረው ክልል ነዋሪ መካከል እምነት እንዳይኖር የማድረግ አላማን ያነገቡ ሀይሎች የሚጠቀሙባቸው መልከ ብዙ የሆነ ይዘት ያላቸው አሉታዊ መረጃዎችን ሲሆኑ ይህንን መሰል ልጥፎች በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በአብዛኛው በአማራ ብልፅግና ፓርቲ ላይ ያለ ምንም እንዲሁም በቂ ማስረጃ የክስ ይዘት ያላቸው መረጃዎች ናቸው። በዚህ ጥናት ላይ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ  የሚወክለውን የአማራ ክልል ማህበረሰብ ሰላም እና ፀጥታ ለማስከበር ፋላጎት የለውም፤ በቅማንት፣ አገው፣ ቤንሻንጉል፣ ኦሮሞ ብሄረሰቦች እና በመስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ቀጥተኛ ጥቃት እያደረሰ ነው፤ በአማራ ማህበረሰብ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚደረሱ ጥቃቶች በቀጥታ እና በተባባሪነት ተሳትፎን እያደረገ ነው፤ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ የስልጣን እርከን የተቆጣጠሩት የአንድ አካባቢ ሰዎች ናቸው፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ አካለት ላይ በተለይም የአብን እና ፋኖ አባላትን በማሰር፣ በማንጋላታት እና በመገደል ላይ ተሳትፎን ያደርጋል ከዚሁ ጋር ተያይዞ የክልሉ ልዩ ሀይል ላይ የተለያዩ ህቡዕ ሴራዎችን እና ቀጥተኛ ጉዳቶችን እንዲደርሱበት በተለያየ መንገድ ይሞክራል የሚሉ ውንጅላዎችን በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ሲሰራጩ ለመታዘብ ተችሏል። በመጨረሻም የአማራ ብልፅግና ፓርቲ አባላት እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ጥቃት እንዲደርስ የሚቀሰቀሱ ብጥብጥ ቀስቃሽ መረጃዎችም በከፍተኛ ደረጃ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ሲሰራጩ ይስተዋላል።

በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚሰራጩትን የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የተመለከቱ አሉታዊ መረጃዎች ስንመለከት ደግሞ በዋነኝነት ሁለት አይነት ባህሪ አላቸው። አንደኛው አንድ ፓርቲ ላይ ብቻ በማተኮር ፓርቲውን በተመለከተ የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ በተለያዩ ፓለቲካ ፓርቲዎች መካከል አለ ወይም ይኖራል ተብሎ በሚታሰበው ርዕዮተ አለማዊ እንዲሁም ፓለቲካዊ እና ማህበራዊ አንድነት እና የአቋም ስምምነት ላይ በመመርኮዝ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ፓርቲዎችን በጣምራ በመጠቀስ በእነሱ ዙሪያ የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች ናቸው። የመጀመሪያውን አይነት ማለትም በተናጠል አንድ ፓርቲ ላይ በማተኮር የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች ስናይ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በዋነኝነት ትኩረት የተሰጣቸው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በቅደም ተከተል አብን (178) ፣ ኢዜማ፣ ባልደራስ፣ እናት ፓርቲ እና ኦፌኮ ናቸው። ሁለተኛው አይነት ማለትም በፓርቲዎቹ መካከል የአቋም ስምምነት/አንድነት አላቸው ተብሎ በጋራ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ በጣምራ በብዛት የምናገኛቸውን ፓርቲዎችን ስናይ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሚጠቅሱ አሉታዊ መረጃዎች ላይ በዋነኝነት የአብን/ባልደራስ (13) ፤ ኢዜማ/ባልደራስ (6) ፤ አብን/ኢዜማ (6) እና አብን/እናት ፓርቲ (1) ጥምረት በብዛት ይገኛል። ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሚጠቅሱ አሉታዊ መረጃዎች ላይ ደግሞ የአብን/ኢዜማ/ባልደራስ (7) ጥምረት በብዛት ይገኛል፤ በተጨማሪም አራት እና ከዚያ በላይ የተቃዋሚ ፓለቲካ ፓርቲዎችን በሚያሰራጩት አሉታዊ መረጃዎች ላይ የሚጠቅሱ የአብን/ኢዜማ/ባልደራስ/እናት (2) እና አብን/ኢዜማ/ባልደራስ/ኦፌኮ ጥምረት (2) በብዛት ይገኛል። ይህም አብዛኛው ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተመለከተ የአሉታዊ መረጃዎች ትኩረት በከፍተኛ ደረጃ አብን ላይ ሲሆን በመቀጠል ኢዜማ እና ባልደራስ ተከታይ ቦታዎችን እንደያዙ የሚያሳይ ነው።

ተፎካካሪ ፓርቲዎችን አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ አብዛኛው አብን የተመለከቱ ሲሆን በይዘት ደረጃ በቀዳሚነት የሚሰራጨው አብን ላይ ክስን የሚያቀርቡ አሉታዊ መረጃዎች ሆነው አግኝተናቸዋል። ከሀሰተኛ መረጃዎች ውስጥ አብንን በተለያዩ ክልሎች በተለይም በቤንሻንጉል፣ አማራ እና ኦሮሚያ በሚደርሱ ግጭቶች ከመንግስት ጋር በጋራ በመሆን እና በተናጠል ቀጥተኛ ተሳታፎ እያደረገ ነው የሚል ይዘት ያላቸው እና ከዚሁ ጋር ተያይዞም አብን በአማራ ክልል በሚኖሩ ሙስሊሞች ላይ ጥቃት እያደረሱ እና እንዲደርስ እየቀሰቀሱ ነው የሚሉ ሀሰተኛ መረጃዎች በቀደሚነት ሲቀመጡ በተጨማሪም የአብንን ፓለቲካ የሚዘውሩት የአንድ አካባቢ ፖለቲከኞች ስለሆኑ ሁሉንም አማራ የሚወከል ድርጅት አይደለም የሚል ይዘት ያላቸው አሉታዊ መረጃዎች በከፍተኛ ደረጃ ሲሰራጩ ለማየት ተችሏል።

በመቀጠል የአሉታዊ መረጃዎች ኢላማ የነበረው የተፎካካሪ ፓርቲ ደግሞ ኢዜማ ሲሆን ኢዜማን የተመለከቱ አሉታዊ መረጃዎችን ስናይ በዋነኝነት በኢዜማ ፓርቲ እና በመንግስት መካከል ከመጋረጃ ጀርባ ስምምነት እንዳለ አድርገው የሚያቀርቡ ሀሰተኛ መረጃዎች ቀዳሚ ሲሆኑ በመቀጠል የኢዜማ ፓርቲ የኢዜማ የፖለቲካ ፓርቲ የአማራ ክልል እንዲፈርስ እና የብሄሩ ተወላጆች እንዲጠፉ በተናጠል እንዲሁም ከሌሎች ጋር በትብብር እየሰራ ነው የሚሉ አሉታዊ መረጃዎች በከፍተኛ ደረጃ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ሲሰራጩ ተስተውሏል።

የተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲዎችን በአንድነት ኢላማ ካደረጉት አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ በአብዛኛው የተለያዩ የመንግስት አካላት እና ተቋማት በእነዚህ ፓርቲዎች ላይ በተለይም የአብን፣ ኢዜማ፣ ባልደራስ እና ኦፌኮ ፓርቲ አባላትን እና አመራሮችን እያንገላቱ፣ እያሰሩ እና እየገደሉ ነው የሚል ይዘት ያላቸው ሀሰተኛ መረጃዎች ሲሆኑ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የተለያዩ የክልል አስተዳደሮች ለተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሞራል ፣ የመሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የሚያተቱ መረጃዎችም በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በከፍተኛ ደረጃ ሲሰራጩ በዚህ ዳሰሳ ላይ ለማየት ተችሏል። በተጨማሪም የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ ማስረጃ የለሽ ክስን የሚያቀርቡ አሉታዊ መረጃዎችም በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በስፋት ሲሰራጩ ለማየት ተችሏል። በተለይም የባልደራስ፣ ኢዜማ እና አብን የፓለቲካ ፓርቲዎች የአንድ ብሄር እና ሀይማኖት የበላይነት እንዲፈጠር የሚፈልጉ ናቸው የሚል ይዘት ያላቸው ሀሰተኛ መረጃዎች ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው።

ማጠቃለያ

በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ ምህዳር ውስጥ የተለያዩ ፓለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች በዚህ ትንተና ላይ ለመዳሰሰ የተሞከረ ሲሆን በዚህ ዳሰሳ ላይ የተለያዩ አዝማሚያዎችን ለመታዘብ ተችሏል። በቀዳሚነት የታዘብነው በፖለቲካ ስልጣን ላይ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የበለጠ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከፍተኛ የአሉታዊ መረጃዎች ኢላማ ሆኖ እንደሚቀርብ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የብሄር ፓለቲካን የሚያራምዱ ድርጅቶች ከሌሎች ፓርቲዎች በተለየ ከፍተኛ የአሉታዊ መረጃዎች አላማ ናቸው። ሁለተኛ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ሀገሪቱ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት እና ህጋዊ ፍቃድ ካላቸው ፓርቲዎች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ትኩረት እንደሚያገኙ እና በማህበራዊ ሚዲያው ላይ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ለመታዘብ ተችሏል። ሶስተኛ ትኩረት ያገኙት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትኩረት ያገኙበት ምክንያት በፓለቲካ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳቸው ሳይሆን አሉታዊ በሆኑና ሴራ ተኮር እንዲሁም በብዛት እርስ በእርስ በሚቃረኑ የመረጃ ስርጭቶች ላይ ነው። አራተኛ አብዛኛው ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የተመለከቱ የማህበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ሀሰተኛ መረጃዎች ሲሆኑ በተጨማሪም የፓለቲካ ስልጣን የያዘ አካል ዙሪያ ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎች በብዛት ሲሰራጩ ይስተዋላል። በመጨረሻም የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች በብዛት ጊዜና ሁኔታዎችን እየተከተሉ የሚለዋወጡ ሳይሆኑ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ አንድ አጀንዳ ላይ ብቻ የማተኮር አዝማሚያ ያላቸው ናቸው።

ምንጭ – Factify Ethiopia

Exit mobile version