Site icon ETHIO12.COM

ግብፅ እና ሱዳንን በተመለከተ በኢትዮጵያ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች

ኢትዮጵያ ካለችበት አካባቢያዊ እና ካላት የተፈጥሮ ሀብት ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ሀገራት ጋር በመልካምም ይሁን በመጥፎ ጎኑ የተለያየ ግኑኝነቶች አሏት። በዋነኝነት ከሱዳን እና ከግብፅ ጋር ያላት ዘመናትን ያስቆጠረ ውስብስብ የሆነ ግኑኝነት ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል። ከሱዳን ጋር በድንበር እና በአባይ ጉዳይ እንዲሁም ከግብፅ ጋር በአባይ ወንዝ የተነሳ ለረዥም ጊዜ የተለያዩ ውዝግቦች እና እስከ ጦርነት የደረሱ ግጭቶች ውስጥ ገብታለች። በተለይም ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አንስቶ እንዲሁም ሀገሪቱ ላለፉት ሶስት አመታት እያለፈችበት ባለው የለውጥ ጉዞ ጋር ተያይዞ በሀገራቱ መካከል ያለው ግኑኝነት እየሻከረ መጥቷል። ይህ ግኑኝነት ከመሻከር አልፎ ከግብፅ ጋር በአለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ላይ እሰጣ ገባ ውስጥ እንዲሁም ከሱዳን ጋር ቀጥተኛ ግጭት ውስጥ ሀገሪቱ መግባቷ ይታወቃል።  በሀገራቱ መካከል የተነሳው ይህ ግጭት እንደ ማንኛውም የ21ኛው ክፍለ ዘመን ግጭት የመረጃ እና የስነ-ልቦና ጦርነት ጎን ያለው ነው። ይህንንም እውነታ ከእነዚህ ሀገራት ጋር ተያይዞ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች ስርጭት ላይ መታዘብ ይቻላል። ግብፅ እና ሱዳንን በተመለከት በኢትዮጵያ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች በብዛት ያሉ ሲሆን ይህ ጥናትም እንደዚህ አይነት ይዘት ያላቸው መረጃዎች ላይ ያተኮረ ነው።

ከ2012 ጀምሮ እስከ መስከረም 2014 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሱዳንና ግብፅን የተመለከቱ 572 አሉታዊ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የተሰራጩ ሲሆን በከፍተኛ ደረጃ እነዚህ መረጃዎች ሲሰራጩ የነበሩት ደግሞ ከየካቲት እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥ ብቻ በአጠቃላይ ከተሰበሰበው መረጃ ውስጥ 75 በመቶ ያህሉ አሉታዊ መረጃዎች ተሰራጭተዋል። ይህም ከትግራይ ጦርነት እና ሱዳን በወረራ የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ የተለያዩ ግዛቶችን ከተቆጣጠረችበት እንዲሁም የአባይን ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ጊዜ ጋር ተመሳሳይነት አለው። ይህ እውነታ የሚጠቁመን የሀገሪቱን ውስጣዊ ሁነቶችን አስታኮ እንደዚህ አይነት ይዘት ያላቸው አሉታዊ መረጃዎች በከፍተኛ ደረጃ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚሰራጩ ነው። (ምስል 1)

ምስል 1: በ2013/14 ዓ.ም የነበረው የአሉታዊ መረጃዎች ስርጭት

ከተሳትፎ እና ተደራሽነት አንጻር በተጠቀሰው ጊዜ ሱዳንና ግብፅ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ አሉታዊ መረጃዎች ከ14,119 ያህል ጊዜ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች አስተያየት ሲሰጡባቸው፤ 39,987 ያህል በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ተጋርተዋል እንዲሁም 86,110 ያህል የስሜት ምላሽ አግኝተዋል። በተጨማሪም እነዚህ መረጃዎች በአጠቃላይ ከ29 ሚሊየን በላይ ለሚቆጠር የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ባላቸው 358 አካውንቶች የተሰራጩ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 56 አካውንቶች በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በአሁኑ ሰዓት ግልጋሎት ላይ የሌሉ ናቸው። ከእነዚህ አካውንቶች ውስጥ 220 የሚሆኑት ብሄር ተኮር መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካውንቶች ሲሆኑ፣ 58 ያህሉ ለመንግስት የወገነ መረጃ የሚያሰራጩ፣ 20 የሚሆኑት የመዝናኛ ይዘት ያላቸውን መረጃዎችን የሚያሰራጩ፣ እንዲሁም 4 አካውንቶች ደግሞ ሀይማኖታዊ ይዘት ያላቸው መረጃዎችን የሚያሰራጩ ናቸው። ብሄር ተኮር መረጃዎችን ከሚያሰራጩት 220 አካውንቶች ውስጥ 90 ያህሉ የአማራ፣ 83 የትግራይ፣ 42 የኦሮሞ ብሄር ላይ የሚያተኩሩ ሲሆን የተቀሩት አካውንቶች የቅማንት፣ ሲዳማ እና ወላይታ ብሄር ላይ የሚያተኩሩ ናቸው።

ከአጠቃላይ ሱዳንና ግብፅን የተመለከቱ አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ 513 ሀሰተኛ መረጃዎች፣ 44 የጥላቻ ይዘት ያላቸው መረጃዎች እና 15 ደግሞ ግጭት ቀስቃሽ ይዘት ያላቸው መረጃዎች ናቸው። ከተለዩት ሀሰተኛ መረጃዎች ውስጥ 436 ያህሉ የፈጠራ ይዘት ያላቸው መረጃዎች ሲሆኑ የተቀሩት 78 ሀሰተኛ መረጃዎች ደግሞ አሳሳች ይዘት ያላቸው ናቸው። ከይዘት አንፃር በዋነኝነት በሚከተሉት ነጥቦች ዙሪያ ያጠነጠኑ ናቸው።

ከላይ በተዘረዘሩት የሀሰተኛ መረጃ ጭብጦች ዙሪያ የሚሳተፉ አካውንቶችን ስናየቸው በዋነኝነት በአንድ ጎን የትግራይ እና ኦሮሞ ብሄር ላይ አተኩረው አሉታዊ መረጃን የሚያሰራጩ አካውንቶች የፌድራል መንግስቱን እና የአማራ ክልልን ሽንፈት እና ውርደት ላይ አተኩረው ሲሰሩ በተቃራኒው የመንግስት አቋምን የሚደግፉ፣ የአማራ ብሄር ላይ አተኩረው የሚሰሩ አካውንቶች የፌድራል መንግስቱን እና የአማራ ክልልን ድል የሚያበስሩ አሉታዊ መረጃዎች ላይ አተኩረው ይሰራሉ። በተጨማሪም የአማራ ብሄር ላይ አተኩረው የሚሰሩ አካውንቶች በፌድራል መንግስት እና በአማራ ክልል ህዝብ መካከል መቃቃርን የሚፈጥሩ ሴራ ተኮር ሀሰተኛ የፈጠራ መረጃዎች ላይ ሲሳተፉ ተስተውሏል።

የጥላቻ ይዘት ካላቸው 44 መረጃዎች ውስጥ 36 ያህሉ አንድን ብሄር ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ መረጃዎች ሲሆኑ የተቀሩት 7 የጥላቻ ንግግሮች ደግሞ የሀገር ክብር እና ስምን የሚያጉድፉ ናቸው። ከይዘት አንፃር ሁሉም የሚያጠነጥኑት ሱዳን የፈፀመችውን ወረራ በማስተካክ የሀገሪቱን እንዲሁም የአማራ ብሄረሰብን ክብር የሚቀንሱ እና የሚያዋርዱ መረጃዎችን መልቀቅ ላይ ነው።

ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑት 15 መረጃዎች ውስጥ 5ቱ አንድ ቡድን ላይ ጥቃት የሚቀስቀሱ፣ 5ቱ የትጥቅ ትግል ጥሪ የሚያደርጉ እና 2ቱ ደግሞ ብጥብጥ ቀስቃሽ የሆነ ይዘት ያላቸው ናቸው። ከይዘት አንፃር ደግሞ እንደ ቡድን ጥቃት እንዲደርስባቸው ከሚያነሳሱት መረጃዎች ውስጥ እንደ ኢላማ ተደርጎ የቀረበው የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ሲሆን የትጥቅ ትግል ጥሪን የሚያደርጉት መረጃዎች ሁሉም የአማራ ማህበረሰብ በመንግስት እና በክልሉ አስተዳደር ላይ እንዲነሳ የሚቀስቅሱ ናቸው።

ማጠቃለያ

በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ ምህዳር ላይ የሚሰራጩ አብዛኞቹ አሉታዊ መረጃዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው። ነገር ግን የተለያዩ የቅርብ እና የሩቅ ሀገሮች ላይ ያተኮሩ ዜናዎችም በማህበራዊ ሚዲያ መድረኩ ላይ በተለያየ አውድ ሲሰራጩ ይስተዋላል። ከእነዚህም መካከል ግብፅ እና ሱዳንን የተመለከቱ መረጃዎች በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዛት በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ። ለዚህም በዋነኝነት ሁለት ምክንያቶች ያሉ ሲሆን አንደኛው ሁለቱም ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳስራቸው ፈርጀ ብዙ እና አወዛጋቢ የሆኑ ጉዳዮች ስላሉ ሁለቱም ሀገራት በኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረጉ የተለያዩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የራሳቸውን ተፅእኖ ለማሳደር የተለያዩ መንገዶችን የሚጠቀሙ መሆናቸው፣ ከነዚህም አንዱ የማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም የመረጃ እና የስነ-ልቦና ጦርነት ውስጥ መግባት እና በሀገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን በማባባስ እና በማጋጋል እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የተለያዩ አካላት ድጋፍ በማድረግ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በየጊዜው ከሚያደርጉት ጥረት ጋር የተያያዘ ነው። ሁለተኛ ምክንያት ደግሞ የተለያየ አላማ ያላቸው በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት እና ግለሰቦች እነዚህ ሀገራትን አሉታዊ መረጃዎችን ለማሰራጨት እንደ ርዕስ እና አጀንዳ አድርገው መጠቀማቸው ነው።  

ምንጭ – Factify Ethiopia

Exit mobile version