Site icon ETHIO12.COM

«በአማራ ክልል የምግብ ዋስትናቸው ያልተረጋገጠ 11 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች አሉ»

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሪት ሰላማዊት ካሳ ከሰጡት መግለጫ ዋና ዋና ነጥቦች

የመንግስት ውሳኔና ሰብአዊ ድጋፎችን በተመለከተ

👉 መንግስት በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ ሲያደረግ ቆይቷል። ከቀናት በፊት ለሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትን ለማፋጠንና በተገቢው መንገድ ለማድረስ እንዲቻል ግጭት የማቆም ውሳኔን አሳልፏል፣

👉 ከትግራይ ክልል በርካታ ዜጎች ወደ አዋሳኝ ክልሎች በተለይም ወደ አማራ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ፍለጋ እየመጡ ነው፣

👉 የአማራ ክልል አካባቢዎች በጦርነቱ ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውና እነሱም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ በከፍተኛ ቁጥር ወደ ክልሉ እየገቡ ያሉትን ዜጎች መደገፍ ከክልሉና ከነዋሪው አቅም በላይ ነው።

👉 ዜጎች ካሉበት አካባቢ ሳይወጡና ሌላ ማህበራዊ ጫና ከመድረሱ በፊት ባሉበት የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ማድረግ ያስፈልጋል፤ የተወሰደው እርምጃ የመንግስትን ቁርጠኛ አቋም በጽኑ የሚያሳይ ነው፤ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ ደግሞ ሌላኛው አካል ለድጋፉ መጓጓዣ እንቅፋት ከሚሆኑ ድርጊቶች መታቀብና በወረራ ከያዛቸውም አካባቢዎች መውጣት ይጠበቅበታል፣

👉 የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ መንግስት ሙሉ ዝግጁና ቁርጠኛ ነው፣

👉 አለም አቀፉ ማህበረሰብ በመንግስት ውሳኔ የሰብአዊ ድጋፎችን ለማድረግ በብዙ መልኩ ፍላጎት እያሳዩ ነው። የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ በተሳለጠ ሁኔታ መድረስ እንዲችል መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋግጣል።

👉 አሁንም አፋጣኝ ድጋፍ ከሚሹት የአማራ ክልል አካባቢዎች ሰሜን ወሎና ዋግ ህምራ ዞኖች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።

👉በአካባቢያቸው በደረሰው ጉዳት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ117 ሺህ በላይ ደርሷል።

👉 በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የነበሩት ዜጎች ቁጥር ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ነበር፤ የፈደራል መንግስትና ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፣

👉አሁንም በአማራ ክልል የምግብ ዋስትናቸው ያልተረጋገጠ 11 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች አሉ፤ ይህንን ለማገዝ መንግስት ከልማት አጋሮችና ከክልሉ ጋር እየሰራ ይገኛል። ሁሉም የማህበረሰብ ክፍልም አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያሻቸው ዜጎች ድጋፉን እንዲያደርግ መንግስት ጥሪ ቀርቧል፣

👉 በአፋር ክልል ጦርነቱ ባደረሰው ጉዳት ሳቢያ በክልሉ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍን ይሻሉ፣

👉 ዳግም ወረራ ከተፈጸመባቸው የአፋር አካባቢዎች ለተፈናቀሉና አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 70 ሺህ ዜጎች ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ የምግብ ድጋፍ ተደርጓል፣

ድርቅና የተጎጂዎች ድጋፍ ‼️

👉 በኦሮሚያ በድርቅ በተጎዱት ዞኖች ሰብአዊ ድጋፍን የሚፈልጉት ሰዎች ቁጥር 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ሆኗል፤ የቦረናና ምስራቅ ባሌ ዞኖች 254 ሺህ ኩንታል ምግብ ድጋፍ በፌደራል መንግስት በኩል በአስቸኳይ ድጋፍ እንዲቀርብ ተደርጎ ለ854 ሺህ ሰዎች ተሰራጭቷል። አንድ ነጥብ 8 ሚሊየን ተጎጂዎች በተለመደው የአደጋ ጊዜ ሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት መንገድ ድጋፉ እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው። 100 የውሃ ማመላለሻ ቦቴዎችን ውሃ አጠር ለሆኑት አካባቢዎች እያቀረቡ ይገኛሉ፣

👉 በሶማሌ ክልል ዝናብ አጠር በሆኑ 9 ዞኖች ውስጥ 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች በድርቁ ተጎጂ ሆነዋል፤ ከተለያዩ አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በክልሉ ለ40 ወረዳዎች 26 ሺህ ኩንታል የምግብ ድጋፍ ተደርጓል፤ የእንስሳት መኖም እንዲሁ የድጋፉ አካል ነው። የውሃ አቅርቦትን የሚሰጡ 159 መኪኖችም በ81 ወረዳዎች የውሃ አቅርቦትን እየሰጡ ይገኛሉ።

ሃገር አቀፍ የህዝብ መድረኮች‼️

👉 በመላ ሃገሪቱ ከወረዳ ጀምሮ በዞንና በከተማ በተለያየ ደረጃ የህዝብ የምክክር መድረኮች ሲካሄዱ ቆይተዋል። በተመረጡ 21 ትልልቅ ከተሞች ደግሞ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባላት በቀጥታ ከህዝብ ጋር ተገናኝተው እንዲወያዩ ተደርጓል። ምክክሮቹን ሲያወያዩ የነበሩት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ለምርጫ ከተወዳደሩበት አካባቢ ውጪ እንዲሄዱ ተደርጎ ነው ። ይህም አንዱ የአንዱ ችግርና ህመም እንዲረዳ አንዱ ማህበረሰብ የሌላውን ጥያቄዎች እንዲያውቅ እድል የፈጠረ ነው።

👉 በተካሄዱት የህዝብ መድረኮች የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ የውሳኔ ሃሳቦችን ማህበረሰቡ እንዲያውቅ ተደርጓል። በዋናነት ግን መድረኮቹ በአሁኑ ወቅት በህብረተሰቡ የሚነሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው የሚለውን ለመሰብሰብ ያለመ ነው። በመፍትሄ እርምጃዎቹም የህብረተሰቡ ሚና ምን መሆን እንዳለበት ለመመካከርም አገዟል። መደማመጥን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ስርአትን ለመገንባት ደግሞ ይህ ትልቅ ጅማሮ ነው። የህዝብ መድረኮቹ ከያዙት አላማ አንጻር በስኬት ተከናውነዋል።

👉ዜጎች ከተሳትፎ ጀምሮ በመድረኮቹ በጣም ጠንካራ ሃሳቦችን ሲያነሱ መንግስት ሊያስተካክላቸው ይገባል ያሏቸውን ሃሳቦች በነፃነት ያነሱበት መሆኑና ሃሳቦቹም ለሁለንተናዊ የሃገር ግንባታ ስራው ትልቅ አስተዋፅኦን የሚያበረክቱ ናቸው። ህብረተሰቡ ጥያቄዎቹን በግልፅ ከማንሳትም ባሻገር መንግስት ለሚወስዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች እገዛ ለማድረግም ቁርጠኝነቱን ያሳየባቸው ስኬታማ መድረኮች ተካሂደዋል።

👉 መንግስት ከነዚህ ምክክሮች የተነሱትን ጥያቄዎች በመያዝ በአፋጣኝ መፍትሄ የሚሰጣቸውን በፍጥነት በማስተካከል፤ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ ለሚፈልጉትም እንዲሁ እንደየ አይነታቸው መፍትሄ ለመስጠት እየሰራ ይገኛል። በነዚህ ህዝባዊ መድረኮች ለተሳተፉ በግልፅነት ጥያቄዎቻቸውን ላቀረቡና ይበጃል ያሉትን ሃሳብ ለሰነዘሩ ሁሉም ኢትዮጵያውያንና ይህንንም ለህዝቡ ለማድረስ ለሰራችሁ መገናኛ ብዙሃን በሙሉ መንግስት ከፍተኛ ምስጋናውን ያቀርባል።

የ HR6600 ሰነድ ጉዳይ‼️

👉 ኢትዮጵያ ላይ በተለያየ መልኩ ጫና ለማሳደር ያቀዱ በርካታ ሙከራዎች ከተለያየ አቅጣጫ ሲሰነዘሩ መቆየታቸውን በተለይ ባለፈው አንድ አመት በግልፅ የተመለከትነው ሃቅ ነው። አሁንም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጫና ለማሳደር የተረቀቀ ነው። በተለይም ሰነዱ በሰሜኑ ጦርነት ትክክለኛ አጥፊው ማን እንደሆነ ያልለየ፤ በጦርነቱ ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን የአፋርና አማራ ክልሎችን ዜጎች ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባና በአንዲት ሉአላዊት ሃገር ላይ የውጭ ጫናን ለማሳደር ያለመ ነው። ሰነዱ በተለይ በፋይናንስ በደህንነት በኢንቨስትመንትና በሰዎች እንቅስቃሴ ማለትም በአሜሪካ ቪዛ አሰጣጥንና በዲቪ ወደ አሜሪካ ለመሄድ የሚሰጠው እድል ላይ ማእቀቦችን ለመጣል ያቀደ ነው። በተጨማሪም በአሜሪካ የሚገኘው ዳያስፖራ በሃገሩ የኢኮኖሚ ተሳትፎና በሬሚታንስ ላይም ከፍተኛ ጫናን የሚጥል ነው። በተለይ አሁን መንግስት በራሱ ተነሳሽነት ለሰላም መስፈንና ሰብአዊ ድጋፎችን ለማድረግ የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ወደ ጎን ያደረገ በመሆኑ ፍትሃዊነት ይጎድለዋል። ይህ ሰነድ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ የሚመነዘር ጫናን ሊፈጥር ይችላል። ከሃገሩ ውጭ ያለውም ዳያስፖራ የዚህ ገፈት ቀማሽ ነው። ለዛም ነው ሁላችንም ይህንን አይነት ጣልቃ ገብነት አጥብቀን ማውገዝ የሚገባን።

👉 መንግስት የተለያዩ የዲፕሎማሲ መንገዶችን በመጠቀም ሰነዱ እንዳይጸድቅ ለማድረግ እየሰራ ነው። መላው ኢትዮጵያዊም ይህ በሃገር ሉአላዊነት ላይ ጣልቃ የሚገባው ሰነድ እንዳይጸድቅ ባለው አቅም ሁሉ ድምጹን ማሰማት ይኖርበታል። በዚህ ወቅት ሃገራችንና ህዝቦቿ በጦርነትና በተፈጥሮ የድርቅ አደጋ እንደውም ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል እንጂ ችግሩን የሚያባብስ ውጫዊ ጫና ፍፁም ፍትሃዊ አለመሆኑን በሃገር ውስጥ ያለውም በውጪ የሚኖረውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለአለም እንዲያሳውቅ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።

Via – EPD

Exit mobile version