Site icon ETHIO12.COM

ኔቶ ከሩስያ ጋር ቀጥተኛ ግጭት ውስጥ እንደማይገባ ዐስታወቀ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የኬሚካል ጦር መሣሪያዎችን ጥቅም ላይ የሚያውሉ ከኾነ ኔቶ «ምላሽ» ይሰጣል ብለዋል። ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ከአውሮጳ ኅብረት እና ቡድን 7 ሃገራት ጋር ቤልጂየም ብራስልስ ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ ካደረገ በኋላ ነው። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ደግሞ፦ ሩስያ «ከባድ ዋጋ» ትከፍላለች ብለዋል። ሆኖም ግን «ዩናይትድ ስቴትስ የኬሚካል ጦር መሣሪያ የመጠቀም አንዳችም ፍላጎት የላትም» ሲሉ አክለዋል።

የሩስያ መንግሥት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ ጆ ባይደን፦ «ትኩረት ለማስቀየስ» እየሞከሩ ነው ሲሉ ወቅሰዋል። ዩክሬናውያን እንደሚሉት ሩስያ በዓለም አቀፍ የተከለከለውን የፎስፈረስ ቦንብ ሰላማዊ ሰዎች ላይ አልተጠቀመችም ሲሉም አስተባብለዋል።

ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከአስቸኳይ ስብሰባው በኋላ ዛሬ ፖላንድን ጎብኝተዋል። ፖላንድ የዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍን በእጅጉ እንደምትሻ ዐስታውቃለች። ጆ ባይደን በፖላንድ ቆይታቸው ኔቶን ለማጠናከር ከሰፈረው የዩናይትድ ስቴትስ 82ኛው አየር ወለድ ብርጌድ ጋር ተገናኝተዋል። ጆ ባይደን ፖላንድ ከዩክሬን 80 ኪሎ ሜትር ወደ ምትርቀው የምሥራቃዊ ፖላንድ ከተማ ርዜስዞውም አቅንተዋል። ፕሬዚደንቱ በፖላንድ ቆይታቸው ከዩክሬን ስለተፈናቀሉ 3.7 ሚሊዮን ሰዎች የሰብአዊ ኹኔታ ማብራሪያ ይደረግላቸዋል ተብሏል።

የአውሮጳ ኅብረት በአስቸኳይ ስብሰባው ሩስያን በጦር ወንጀለኝነት ፈርጇል። ሆኖም የዩክሬን ፕሬዚደንት እንደሚፈልጉት በሩስያ ላይ ኔቶም ሆነ ሌሎች ኃያላን ሃገራት አጠቃላይ ማዕቀብ ግን አልተደረገም። በዩናይትድ ስቴትስ ርዳታ የአውሮጳ ኅብረት ከሩስያ የኃይል አቅርቦት ጥገኝነት ለመላቀቅ ግን ቃል ገብቷል። ዋሽንግተን በያዝነው የጎርጎሪዮሱ ዓመት 2022 እስከ 15 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ነዳጅ የአውሮጳ ኅብረት እንዲያገኝ ለማረጋገጥ እንደምትሠራም ፕሬዚደንቱ ቃል መግባታቸውም ተገልጧል።

Exit mobile version