Site icon ETHIO12.COM

በበርሜል ነዳጅ ሲሸጡ የተገኙ ሶስት ማደያዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

በበርሜል ነዳጅ ሲሸጡ የተገኙ ሶስት ማደያዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አሰታወቀ


ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በፈጠሩና በምሽት በበርሜል ነዳጅ ሲሸጡ የተገኙ ሶስት ማደያዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ተናገሩ።

መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገባቸው ምርቶች መካከል ነዳጅ መሆኑን የለለጸው ቢሮው ከስርጭት ጋር ተያይዞ አንዳንድ ማደያዎች የሚፈጥሩትን እንግልትና ሻጥር ፈር ለማስያዝ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደሚወስድና ብልሹ አሰራርን እንደማይታገስ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ከነዳጅ ማደያ ባለሃብቶች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ከስርጭት ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ማደያዎች የሚፈጠረው ብልሹ አሰራር፥ የምርት ስርጭት ፈተና መሆናቸውን አብራርተው ፥ያልተገባ ጥቅም በመፈለግ እጥረቱን በሚያባብሱ የነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስረድተዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል የነዳጅ አቅርቦትን በማሳደግና ቁጥጥሩን በማጠናከር ሌሊት ነዳጅ በሚሸጡት ላይ የመጠን ማሻሻያ እንደሚደረግና በዘመናዊ የመረጃ ዘዴ ማደያዎች እለታዊ መረጃን ለቢሮው እንዲያሳውቁ ማድረግ የሚያስችል አሰራር የሚዘረጋ መሆኑንም የጋራ መግባባት ላይ መድረሱን ከከንቲባ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በከተማዋ ከ134 የነዳጅ ማደያዎች 117 ማደያዎች አገልግሎት እየሰጡ ነው። ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በፈጠሩና በምሽት በበርሜል ነዳጅ ሲሸጡ የተገኙ ሶስት ማደያዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰዱን አቶ አደም ኑሪ ተናግረዋል፡፡

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version