Site icon ETHIO12.COM

በሱዳን ዳርፉር የጦር ወንጀል ተጠርጣሪዎች በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው

በሱዳን ዳርፉር የተፈጸሙ ወንጀሎች እና የመብት ጥሰቶች ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ሊዳኙ መሆኑ ተገልጿል። 

በቀድሞው የሱዳን መንግሥት ድጋፍ ይደረግላቸው የነበሩት የጃንጃዊድ ሚሊሻ መሪ የነበሩ ተጠርጣሪ በጦር ወንጀልና ኢሰብአዊ ጭካኔዎችን በመፈጸም በሚል ክስ ስር 31 መዝገቦች ተከፍተውባቸዋል። 

የቀድሞው መሪ አሊ ሙሀመድ አል አብድ አል ረሃም ግን የቀረበባቸውን ክስ ተቃውመዋል። በሌላ በኩል የሱዳን የመብት ተሟጋቾች ግን የሰውዬው ፍርድ ቤት መቅረብ ታሪካዊ እንደሆነ ገልጸዋል። 

‘’የዛሬዋ ቀን በዳርፉር ጥቃት ለደረሰባቸውና ተርፈው አሁን አብረውን ላሉ ሱዳናውያን ትልቅ የድል ቀን ነው’’ ሲሉ ተደምጠዋል በሱዳን የሰብአዊ መብቶች ጠበቃ የሆኑት ሞሳድ ሞሀመድ አሊ። ‘’ ሙሀመድ አል አብድ አል ረሃም ለፈጸሙት ጭካኔ የተሞላበት ተግባርና ጾታዊ ጥቃት ተገቢውን ፍርድ እንደሚያገኙ ተስፋ አደርጋለው’’ ሲሉም አክለዋል። 

አሊ ኩሻይብ በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት የቀድሞው የጃንጃዊድ ሚሊሻ መሪ 300 ሺ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት እንዲሁም ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ካደረገው የዳርፉር የእርስ በርስ ጦርነት ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የቀረቡ የመጀመሪያው ግለሰብ ናቸው። 

ምንም እንኳን የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር አል በሽር ግን እስካሁን ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ባይውሉም በ2019 ከተካሄደው የመፈንቅለ መንግሥት በኋላ ግን በመንግሥት ቁጥጥር ስር ናቸው ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው። 

እንደዘገባው የቀድሞው መሪ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በዘር ማጥፋት ወንጀልና በጦር ወንጀል ይፈለጋሉ። የቀድሞው የጃንጃዊድ መሪ ሻመሪ አሊ ሙሀመድ ደግሞ ለ13 ዓመታት በሽሽት ቢኖሩም በአውሮፓውያኑ 2020 ላይ እራሳቸውን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አሳልፈው ሰጥተዋል። 

ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል በአውሮፓውያኑ ከነሃሴ 2003 እስከ መጋቢት 2004 ባሉት ወራት ውስጥ የንጹሃን ዜጎች መኖሪያ መንደሮች ላይ ጥቃት መፈጸምና መሳተፍ አንደኛው ነው። 

ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤቱ እንደሚለው በእርሳቸው ስር የነበሩ ወታደሮች መድፈር፣ ከባድ ማሰቃየት፣ ግድያ እና ዝርፊያ ፈጽመዋል። የቀድሞው መሪ ከዚህ በፊት ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት በስህተት ክስ እንደመተሰረተባቸው መግለጻቸውን ሬውተርስ የዜና ወኪል መዘገቡ የሚታወስ ነው። 

በአውሮፓውያኑ 2003 ሱዳን ዳርፉር ውስጥ ግጭት ሲቀሰቀስ በብዛት አረብ ያልሆኑት ዜጎች ከመንግሥት በተቃራኒው በመቆም የትጥቅ ትግል ማድረግ ጀምረው ነበር። ምክንያታቸው ደግሞ መንግሥት እያገለላቸው መሆኑ እና አካባቢው ምንም አይነት እድገት አለማሳየቱ ነው። 

መንግሥት ደግሞ ለዚህ ምላሽ ለመስጠት በሚል በአካባቢው የሚገኙ የአረብ ሚሊሻዎችን (ጃንጃዊድ) በማደራጀትና በማሰልጠን ከአማጽያኑ ጋር እንዲዋጉ አደረገ። 

በዚህም ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ሕይወታቸው ሲያልፍ ሚሊየኖች ደግሞ ተፈናቅለዋል። በወቅቱም ይህ ጉዳይ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል። በአይሲሲ ክስ ከቀረበባቸው መካከል አሊ መሃመድ አሊ አብድ አልራህማን ይገኙበታል::

በጋዜጣው ሪፖርተር 

አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2014

Exit mobile version