Site icon ETHIO12.COM

የደቡብ ክልል – የሕዝብ ጥያቄዎችን በዘጠና ቀናት ውስጥ ለመፍታት…

የሕዝብ ጥያቄዎችን በዘጠና ቀናት ውስጥ ለመፍታት የሚያስችል እቅድ መዘጋጀቱን የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ተናገሩ፡፡

አቶ ጥላሁን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ መጋቢት 14 በክልሉ 157 የሚደርሱ ከተሞች በልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል፡፡

በማህበረሰቡ ዘንድ በይደር የቆዩ ጥያቄዎች የሚፈቱበትን አቅጣጫና ስልት ለመቀየስ እንዲሁም ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ታልሞ በተከናወነው ሕዝባዊ የውይይት መድረክ በርከት ያሉ ግብዓቶችን በመቀመር በሚቀጥሉት ሶስት ወራት የማህበረሰቡን ጥያቄዎች ተደራሽ ለማድረግ እቅድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡ እቅዱ በዋናነት ማህበረሰቡ በልማት፣ መልካም አስተዳደር፣ የጸጥታና ደህንነት፣ እንዲሁም ከኑሮ ውድነት ጋር የተያያዙ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መሰረት በማድረግ የተዘጋጀ የዘጠና ቀናት እቅድ ሲሆን ይህም ከሚያዝያ አንድ እስከ ሰኔ ሰላሳ ድረስ የሚቆይ መሆኑን አቶ ጥላሁን ጠቅሰዋል።

በተለይም የፓርቲውን የውስጥ አቅምንና ጥንካሬ በማጎልበት፤ በመንግሥት ደረጃ መፈታት የሚችሉ ተግባራትን በመፍታት እንዲሁም ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በፍጥነት በማየት በጊዜና በምክንያታዊነት መፈታት የሚችሉ ችግሮችን ባለማሳደር በፍጥነት እንዲፈቱ ለማድረግ አቋም መወሰዱን ተናግረዋል።

የተነሱ ልዩ ልዩ ችግሮችን እንደየ ከተሞቹ ባህሪና ልዩነት ተለይቶ በስምንት ግቦች በማስቀመጥ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት መጠናቀቁን ያብራሩት ኃላፊው፤ በሂደቱም የሚከወኑ መደበኛ ተግባራት ሳይቋረጡ ጊዜ የማይሰጣቸውን የማህበረሰቡ አንገብጋቢ ችግሮች በተለይም ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ማነቆዎችን ለመፍታት የማስተካከያ እርምጃዎች መወሰድ መጀመራቸውን አቶ ጥላሁን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ከሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ከማህበረሰቡ ደህንነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ሰፋፊ ቅሬታዎችን ከመመልከት አኳያም የሕዝቡን ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ የታጠቁና ያልታጠቁ አካላትን ከህዝቡ ጋር በመሆን የመለየት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። በዚህ ረገድ እጃቸው ያለበት የጸጥታ አካላትን የመፈተሽ እና በዛው ልክ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። በዚህም ሂደት ፖለቲካዊ እርምጃዎችን ከመውሰድ ጎን ለጎን ጥፋተኛ የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ኮሚቴ በማዋቀር የማጣራት ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ለወጣቱ የሥራ እድል መፍጠር ትኩረት ከሚሰጣቸው ተግባራት ዋነኛው መሆኑን የገለጹት አቶ ጥላሁን፤ የኑሮ ውድነት ችግርን ለመቅረፍ በከተማ ግብርና ማዕቀፍ በተቀመጠው አቅጣጫ ለመተግበር በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። የገጠሩ ማህበረሰብም ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ግብዓት በማቅረብ ትርጉም ባለው መንገድ ለመተግበር የክልሉ መንግሥት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመላክተዋል።

ከዚህ በፊት በየጊዜው የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት ቃል ከተገባ በኋላ የሚረሱ ጥያቄዎች እንደነበሩ ያስታወሱት ኃላፊው፤ በዚህ የእቅድ ትግበራ የሚድበሰበሱ ጥያቄዎች እንደማይኖሩና እንደሚፈቱ አንስተዋል። መፈታት የማይችሉና ጊዜ የሚወስዱ ጥያቄዎች ደግሞ ለሕዝብ ግልጽ በማድረግ ከተጠያቂነት ጋር ተወስደው እንደሚተገበሩ ገልጸዋል።

ፍቃዱ ዴሬሳ 

አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2014

Exit mobile version