Site icon ETHIO12.COM

ደብረጽዮንና ጌታቸውን ጨምሮ 37 ተከሳሾች በመገናኛ ብዙሃን ጥሪ እንዲደረግላቸው ታዘዘ

ፍርድ ቤቱ በዶክተር ደብረጽዮን የክስ መዝገብ የተካተቱ ተከሳሾች በመገናኛ ብዙሃን እንዲጠሩ ትእዛዝ ሰጠ


የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዶክተር ደብረጽዮን የክስ መዝገብ የተካተቱ ተከሳሾች በጋዜጣና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ጥሪ እንዲደረግላቸው ትእዛዝ ሰጠ።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ በትግራይ ክልል ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን ጨምሮ በመዝገቡ የተካተቱት 37 ተከሳሾችን አፈላልጎ ማቅረብ እንዳልቻለ ለፍርድ ቤት ገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ ተከሳሾቹ ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይልኝ ለማድረግ የጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግ ይፈቀድልኝ ሲል አቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ-ሽብርና ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ተከሳሾች በጋዜጣና በኢቢሲ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በችሎቱ በዚሁ መዝገብ ሥር የተካተቱት ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ዶክተር አዲስዓለም ባሌማ፣ ዶክተር አብርሃም ተከስተን ጨምሮ 17 ተከሳሾች በችሎቱ ተገኝተው ጉዳያቸውን ተከታትለዋል።

ቀሪዎቹ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልንና የሕወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 37 ተከሳሾች በቁጥጥር ሥር እንዳልዋሉ ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱ ፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ላልዋሉት ተከሳሾች መጥሪያ እንዲያደርስ በተደጋጋሚ ትእዛዝ የሰጠ ቢሆንም ፖሊስ በክልሉ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ትእዛዙን መፈፀም አልቻልኩም በማለት ቀርቦ ለችሎቱ አስረድቷል።

ችሎቱ በወንጀለኛ መቅጫ 162/1 መሠረት በቁጥጥር ሥር ያልዋሉትን 37 ተከሳሾች በጋዜጣና በኢቢሲ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዛዝ ሰጥቷል።

ችሎቱ የተፈቀደውን የጋዜጣና የቴሌቪዥን ጥሪ ምላሽ ለመጠባበቅ ለግንቦት 08 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

በዶክተር ደብረጽዮን የክስ መዝገብ በሽብር ወንጀል ከተከሰሱ 62 ሰዎች መካከል ስብሃት ነጋ፣ ሙሉ ገብረእግዚአብሔርን ጨምሮ ስድስት የሕወሓት አመራሮች በመንግሥት ክሳቸው መቋረጡ ይታወሳል።

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version