Site icon ETHIO12.COM

“ጉዳዩ መሬት የመያዝ እንጅ የሀይማኖት አይመስልም” – “ታቦቱ ከቦታው አልነሳ አለን”

” ተቆፍሮ የተገኘውን ታቦት” አቅራቢያ ወዳለው ቤ/ ክርስቲያን አስጠጉት እንጂ እዚህ መሆን አይችልም” የገላን ከተማ – “ታቦቱ ከቦታው አልነሳ አለን” መልስ

“ጉዳዩ መሬት የመያዝ እንጅ የሀይማኖት አይመስልም”
(የገላን ከተማ ከንቲባ)

በገላን ከተማ ታቦት ከመሬት ተቆፍሮ ወጥቷል የሚል መረጃ ከሰሞኑ በማኅበራዊ ትስስር ገፆች ሲዘዋወር ነበር።

ጉዳዩን አስመልክቶ ምላሽ የጠየቃቸው የገላን ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ወይንሸት ግዛው መጀመሪያ ላይ በስፍራው ጸሎት እናድርግ ብለው ግለሰቦች ፍቃድ የገላን ከተማ አስተዳደር መጠየቃቸውንና “ለፀሎት የሚሰጥ ፍቃድ ስለሌለ” ጸሎት ማድረግ ትችላላችሁ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለሁለተኛ ጊዜ በጻፉት ደብዳቤም ታቦት እንደተገኛና በስፍራው መቆየት አለበት ቢሉም አስተዳደሩ በበኩሉ ይህ እንደማይሆንና በአቅራቢያው ወደሚገኝ ቤተ ክርስቲያን እንዲወስዱት ምላሽ ሰጥተናል ይላሉ ከንቲባዋ።

“ለሁለተኛ ጊዜ በጻፉት ደብዳቤ ታቦቱን በጨፌቱማ ካላቆየነው በስተቀር አልነሳ ብሎናል አሉ። ይሄንን ደግሞ እኛ አላመንበትም። እኔም የሃይማኖቱ ተከታይ ነኝ። ግን እንዲህ ያለ ነገር አላውቅም።” ብለዋል።

ታቦቱ ተገኘ በሚባልበት ቦታ አቅራቢያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስለሚገኝ ታቦቱን ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወስደው ፀሎታቸውን መቀጠል እንደሚችሉ እንደነገሯቸው ከንቲባዋ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ካለበለዚያ ግን በፖሊስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ማስጠንቀቃቸውን” ገልጸዋል።

ሆኖም “በአካባቢው ያሉት ሰዎች ጳጳስ ካልመጣ በስተቀር ታቦቱ አይነሳም ብለው እስካሁን እዛው እንደተቀመጡ ነው።” ብለዋል።

ከንቲባዋ እንደሚሉት ተገኝቷል በተባለው ታቦት ዙርያ የተሰበሰቡት ሰዎች ከሌላ አካባቢ ወደ ገላን ከተማ የሄዱ ናቸው።

የከተማ መስተዳድሩ በአሁኑ ወቅት ቦታውን ይሰጣቸዋል ወይ? ሲል ቢቢሲ ለከንቲባዋ ጥያቄ የሰነዘረላቸው ሲሆን እሳቸውም በምላሹ።

“ይህንን አንፈቅድም። ቦታውን መንግሥት ለፕሮጀክት ይዞታል። ዲዛይን ወጥቶለታል። ስለተቀመጡበት ብቻ የሚፈቀድ መሬት የለም።” ብለዋል ከንቲባዋ

ግለሰቦቹ በደብዳቤ መሬቱ እንዲሰጣቸው እንደጠየቁና ይህ መሬትም ስለማይሰጥ ደብዳቤውን መልሰው እንዲወስዱ መንገራቸውን አስረድተዋል።

“ጉዳዩ መሬት የመያዝ እንጂ የሃይማኖት አይመስልም። ከዚህ ቀደም ፀበል አገኘሁ ያለን ሰው አስቁመን ግለሰቡ ታስሯል።” ብለዋል ከንቲባዋ

Exit mobile version