Site icon ETHIO12.COM

ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ምንነትና ልዩ ባህሪያት

“ወንጀሉ በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር በተሻገረው ሰው ላይ ሞት አስከትሎ እንደሆነ አሻጋሪው እስከ ሞት በሚደርስ ቅጣት ሊቀጣ እንደሚችል በህጉ ተደንግጎ ይገኛል”

ሰላም ጤና ይስጥልን ውድ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የማህበራዊ ትስስር ገጾቻችን ተከታታዮች ባለፈው ሳምንት በሰው መነገድ ወንጀል ምንነት ላይ አንድ ጥርቅር ወደ እናንተ ማድርሳችን ይታወሳል ታዲያ በክፍል ሁለት ፕሮግራማችን ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ምንነትና ልዩ ባህሪያት በሚል ርዕሰ-ጉዳይ አንድ ጥንቅር ልናቀርብላችሁ ቀጠሮ ይዘን በተለያየነው መሰረት በዛሬው ጥንቅራችን ስለ ጉዳዩ በፍትህ ሚኒስቴር በብሄራዊ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ውስጥ ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ ከሆኑት ከአቶ አቤል ገ/እግዚሀበሔር ጋር ቆይታ አድርገን ተከታዩን ማብራሪያ ሰጠውናል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ሲባል ምን ማለት ነው?

ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል እንደ በሰዎች የመነገድ ወንጀል ሁሉ በባህሪዉ ድንበር ተሻጋሪ እንዲሁም በተደራጁ ቡድኖች ሊፈፀም የሚችል ነዉ ሲሉ አቶ አቤል ማብራሪያቸውን ይጀምራሉ ወንጀሉ በሀገራት ልዋላዊነት ላይ የሚፈጸምና የተጎጂዎችን ስምምነት መሰረት አድረጎ መፈጸሙ የልዩ ባህሪው መገለጫ መሆኑን ያነሱት ዐቃቤ ህጉ ይህም ሁኔታ በሰው ከመነገድ (ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር) የሚለየው ዋንኛ ምክንያት ነው ይላሉ። በሰው የመነገድ ወንጀል በሰዎች ሰብዓዊ ክብር ላይ የሚፈጸምና የተጎጂው ፍቃደኝነትም የሌለው ወይም ቢኖረውም በህግ ፊት ተቀባይነት የሌለው መሆኑ ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል የሚለየው ጉዳይ መሆኑንም ያነሳሉ።

በመሆኑ የአለም ሀገራት ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ ወንጀሉን በጋራ ለመከላከል እንዲያስችላቸዉ ፍልሰተኞችን በየብስ፣ በባህር እና በአየር ማሻገርን የሚከለክለውን የስምምነቱ ድጋፍ ፕሮቶኮል በመፈረም በመተግበር ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ እኛም ከተል አድርገን ለመሆኑ ፕሮቶኮሉ ዓላማ አድርጎ የተነሳው ምንድን ነው ብለን ጥያቂያችን አነሳንላቸው እሳቸውም ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተውናል፡-

ይህ ሰዎችን በህገ- ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ፕሮቶኮል አላማዉ አድርጎ የተነሳዉ
ሰዎችን በህ-ገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣
ለዚሁ አላማ የአባል ሀገራትን ትብብር ማጠናከር እና
ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ተጎጂዉችን መብት ለማስጠበቅ ነዉ ሲሉ አላማውን ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያም በአዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 8 መሰረት ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ተፈፀመ የሚባለው ማንኛዉም ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገንዘብ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ፡-

ሰዉን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንዲገባ ካደረገ፣
ከኢትዮጲያ ግዛት እንዲወጣ ካደረገ፣
በኢትዮጵያ ግዛት እንዲተላለፍ ካደረገ፣ ወይም ሰውን ከኢትዮጵያ ግዛት ለማስወጣት ዝግጅት ያደረገ፣ በሂደት ላይ የተገኘ፣ ያጓጓዘ ወይም የተቀበለ እንደሆነ ነው ሲሉ በአዋጁ ላይ የተካተቱ ሀሳቦችን ዋቢ አድርገው ያነሳሉ፡፡

ከቅጣት ጋር ተያይዞ ላነሳንላቸው ጥያቄ ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት ፈጽሞ የተገኘ አካል ከ5 ዓመት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ10 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይጠብቀዋል ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ከላይ እንደተመለከተው በአዋጁ መሰረት ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ማቋቋሚያዎች ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ድርጊትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው ፕሮቶኮል ለወንጀሉ ካስቀመጣቸው ማቋቋሚያዎች ጋር ተመሳሳይ ናቸውም ብለዋል፡፡ ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል በሰው ከመነገድ ወንጀል የሚለየው በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ (በስምምነት የሚፈፀም) መሆኑ፣ ሁልጊዜም ድንበር ተሻጋሪ መሆኑ እና በሰው የመነገድ ወንጀል በአገር ውስጥም ሊፈፀም የሚችል መሆኑ፣ ወ.ዘ.ተ ይገኝበታልም ሲሉ ልዩ ባህሪውን ያብራራሉ፡፡

የወንጀሉ ማክበጃ ሁኔታዎችን በተመለከተም ተከታዩን ማብራሪያ አስቀምጠዋል፡-

በአዋጁ አንቀጽ 8 ስር እንደተመላከተው ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ማክበጃ ተደርገው የተወሰዱት የወንጀሉ አፈጻፀም ሁኔታ፣ የተጎጅዎች ሁኔታ እና እድሜ እንዲሁም የወንጀል ፈጻሚው ማንነት ሲሆኑ ማክበጃዎቹና የተቀመጠላቸው ቅጣትም ወንጀሉ የተፈፀመው፡-
በሕጻናት፣ በአዕምሮ ህመምተኛ ወይም በአካል ጉዳተኛ ላይ ከሆነ፤
አደንዛዥ ዕፅ፣ መድሃኒት ወይም የጦር መሣሪያ በመጠቀም እንደሆነ፤
በመንግስት ሠራተኛ ወይም በባለሥልጣን ከሆነና ወንጀሉን የፈጸመው የተሰጠውን ኃላፊነት መከታ በማድረግ ከሆነ፤ ወይም
የአገር ውስጥ ወይም የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ፈቃድ ባለው አካል ፈቃዱን ሽፋን በማድረግ እንደሆነ፤ ከ7 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከ20 ሺህ እስከ 150 ሺህ ብር በሚደረስ መቀጮ የሚቀጣ ሲሆን የወንጀል ድርጊቱ፣
በተጎጂው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት፣ የማይድን በሽታ ወይም ዘላቂ የአዕምሮ ጉዳት ካስከተለ፣
የተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል በመሆን ወይም ቡድኑን በመምራት ወይም በማስተባበር ከተፈፀመ፤
የተጎጂው ህይወት ወይም ደህንነት አደጋ ላይ የወደቀ ወይም ለኢ-ሰብአዊ አያያዝ የተዳረገ እንደሆነ ከ10 ዓመት እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከ30 ሺህ እስከ 150 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ የሚቀጣ ሲሆን፣

በተጨማሪም ወንጀሉ በተጎጂው ላይ ሞት አስከትሎ እንደሆነ ከ15ዓመት እስከ 25 ዓመት ወይም እድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞት እና ከሃምሳ ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል ሲሉ የቅጣቱን ማክበጃ ምክኒያቶች በዝርዝር አቃቤ ህጉ ያስቀምጣሉ፡፡

ውድ ተከታታዮቻችን ለዛሬ ያዘጋጀንላችሁ ጥንቅር በዚሁ አበቃን ዐቃቤ ህጉን ከኛ ጋር ላደረጉት ቆይታ እያመሰገንን በቀጣይ በሌላ ጥንቅር እስክንገናኝ ሰላም፡፡

Via – Attorney general

Exit mobile version