Site icon ETHIO12.COM

በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተላከው አጣሪ ኮሚቴ በፈተና አስተራረም ዙሪያ የደረሰበትን ሂደት ይፋ አደረገ።

የትምህርት ሚኒስቴርና የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ኤጄንሲ የ12ኛ ከፍል ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ውጤት ማስታወቃቸው ይታወሳል። የመግቢያ ፈተናው ውጤት ይፋ ከተደረገ በኋላ በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በወላጆች እና በተቋማት ጭምር ቅሬታ ፈጥሯል። የፈተና ውጤቱ የአስተራረም ስህተት አለበት፣ በጦርነቱ ውስጥ የነበሩ አካባቢዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም የሚሉ ቅሬታዎች ተነስተውበታል።

አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በአማራ ክልል ወረራ ፈፅሞ ቆይቷል፣ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች የትምህርት ተቋማትን ዘርፏል፣ አውድሟል፣ ተማሪዎችም ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል። የሽብር ቡድኑ በወገን ጦር ተመትቶ ከወረራቸው አካባቢዎች ለቅቆ ሲወጣ ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት ሳይወስዱ፣ በጦርነት ምክንያት ያጧቸውን ወገኖች ሀዘን ሳይወጡ ለፈተና ተቀምጠዋል። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የተፈተኑት ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ ሲማሩ ከከረሙ፣ ሥነ ልቦናቸው ከተጠበቀላቸውና ትምህርት ቤቶቻቸው ምንም አይነት ጉዳት ካልደረሰባቸው ተማሪዎች ጋር እኩል ተመዝነዋል። ይህ ደግሞ የተማሪዎችን ችግር ያገናዘበ አይይለም ነው የተባለው።

በአማራ ክልል በ12ኛ ክፍል የፈተና አስተራረም ዙሪያ የተነሳውን ቅሬታ ለማጣራት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አጣሪ ኮሚቴ መላኩ ይታወሳል። አጣሪ ኮሚቴው የደረሰበትን ሂደት በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የኮሚቴው ሰብሳቢ ሙላው አበበ ፈተናው በአማራ ክልል ያለምንም ችግር ተጠናቅቆ እንደነበር አስታውሰዋል። ፈተናው ታርሞ ውጤት ሲታይ ችግር ስለነበር ሳይስተካከል መለቀቅ የለበትም የሚል ቅሬታ ትምህርት ቢሮው ማቅረቡንም አስታውሰዋል። የተነሱ ችግሮች ሳይጣሩ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ መቆረጥ እንደሌለበት መግለፃቸውንም ተናግረዋል።

የውጤት መቀያቀርና የፈተና አስተራረም ስህተት ስለነበር አጣሪ ኮሚቴ ይዘው መሄዳቸውንም አስታውቀዋል። በትምህርት ቤታቸው ጎበዝ የነበሩ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ውጤት ያላመጡበት ምክንያት፣ አንዳንድ ተማሪዎች በአንድ ትምህርት ከፍ ያለ ውጤት በአንደኛው ደግሞ የወረደ ያመጡበትን፣ ምንም አይነት ተማሪዎች ያላስገቡ ትምህርት ቤቶችንና የውጤት መቀያየር ለምን ኖረ? የሚለውን ይዘው መሄዳቸውንም ገልፀዋል። የዩኒቨርሲቲ መግቢያ በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች ታሳቢ ያደረገ አይደለም የሚለው ጥያቄም ሌላው ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዋል።

ማሽኑን አናምንም ብለን በእጃችን ሁሉ አርመን አረጋግጠናል፣ የውጤት አገላለፁ ምን ያክል ትክክል ነው የሚለውንም አይተናል ነው ያሉት በመግለጫቸው። የፈተና ቡክሌት መቀያየር ችግር እንደተመለከቱም ገልፀዋል።ምንም ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶችን ርእሰ መምህሩን በመውሰድ ጎበዝ ተማሪዎችን በእጃችን ሁሉ የማረም ሥራ ሠርተናል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ተማሪዎች ውጤት መቀነሱ በጦርነት ምክንያት የሥነ ልቦና ችግር ስለነበረባቸው ነውም ብለዋል። እነዚህን ተማሪዎች ከሌሎች ተማሪዎች ጋር እኩል መመዘን ፍትሐዊ አለመሆኑን ቢሮው መጠየቁንም ገልፀዋል። ከሲቪክስ ውጤት በተጨማሪ በሌሎች ላይም ጥርጣሬ አለን መታየት አለበት የሚል ጉዳይ ማቅረባቸውንም ገልጸዋል።

ፈተናዎች ወጥተዋል የሚል ወሬ በመናፈሱ ተማሪዎች ሳይረጋጉ መፈተናቸው በውጤታቸው ተፅዕኖ መፍጠሩንም ገልፀዋል።

የትምህርት ቢሮው ኃላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ.ር) እየተነሱ ያሉ ጉዳዮችን ያለ እረፍት እየተከታተሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የክልሉ ተማሪዎች ያላቸው አቅም ይታወቃል ያሉት ኃላፊው ነገር ግን በተማሪዎች ውጤት ላይ የታየው የውጤት ማሽቆልቆል የተጠበቀ እንዳልነበር ተናግረዋል። ለውጤት ማሽቆልቆል ምክንያት የፈተና አስተራረም ችግር፣ በሌሎች አካባቢዎች አብላጫ እድል ተወስዶባቸው ይሆናል የሚልና ጦርነቱ ያመጣው ችገር ይሆናል የሚል ጉዳዮችን ይዘው መሥራታቸውንም ተናግረዋል።

የተቋቋመው ኮሚቴ ያገባኛል ከሚሉ አካላት የተውጣጣ መሆኑንም ገልፀዋል። በቴክኖሎጂ ችግር እንዳይፈጠር የሶፍት ዌር ባላሙያ ጭምር በኮሚቴው መካተቱን ተናግረዋል። ቢሮው በትኩረት እየሠራበት መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ማተብ ዝም ብሎ የራስን ሃሳብ ብቻ ማቅረብ የሕዝብ ጥያቄም አልመለሰም፣ ሕዝብም አላዳነም ነው ያሉት።

ትምህርት ሚኒስቴርም ኮሚቴው ማጣራት የሚገባውን ጉዳይ እንዲያጠራ ትብብር ማድረጉንም አስታውቀዋል። እንደሲቪክስ በጣም የወጣ ባይሆንም በሌሎች የትምህርት አይነቶችም ጥርጣሬ መነሳቱንም ተናግረዋል።

በተነሱ ችግሮች በተደረገ ውይይት በትምህርት ስርዓቱ ላይ ያለው የእምነት መላላት እንዲስተካከል መስማማታቸውን ገልፀዋል።

የፈተናዎች ስርቆት መኖሩንም በተደረገው ውይይት መገለፁን እና ከዚህ አዙሪት ለመውጣት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ መግባባታቸውንም ተናግረዋል።

የአማራ ክልልን ከማንም ክልል ጋር ሳናወዳድር በራሱ ክብረ ወሰን ነው ያወዳደርነው ያሉት ዶክተር ማተብ በአንድ ዓመት እንደዚህ አይነት የውጤት ማሽቆልቆል ሊፈጠር እንደማይችል ዝርዝር ጉዳይ ማቅረባቸውን ገልፀዋል። በተደረገው ውይይት ጦርነቱ በተማሪዎች ውጤት ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉን መስማማታቸውንም አስታውቀዋል። ውሳኔው ደግሞ ከፍ ባሉ አካለት እንዲሰጥ መግባታቸውንም አንስተዋል። እኛ ጥያቄ ያቀረብነው ተማሪዎች አማራ ስለሆኑ ሳይሆን ችግር ውስጥ ስለነበሩና ችግሩን በግልጽ ስለምናውቀውና ስለነበርንበት መታየት ስላለበት ነው ብለዋል።

ለሚነሱ ችግሮች እንደሚታገሉም አረጋግጠዋል። በሕልውና አደጋ ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች ለፈተና ሲዘጋጁ ነበር ብሎ መከራከር እንዳማይቻልም ገልፀዋል። የአማራ ክልል ወጣቶች በጦርነቱ ምክንያት ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ መልኩ በሕልውና ዘመቻው ተሳትፈዋል። በርካታ መምህራን በጦርነቱ ተሳትፈው ተሰውተዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የነበረ ተማሪ ተረጋግቶ ተፈትኗል ማለት አይቻልም፤ ይህን ሰው የሆነ ሁሉ እንዲረዳው እንፈልጋለን፣ ኢትዮጵያውያን በዚህ ልክ እንዲረዱን እንፈልጋለንም ብለዋል።

ጦርነቱ ከፍተኛ የሆነ ችግር አድርሷል ይህ ሊታመን ይገባልም ነው ያሉት። በአስከፊ ጦርነት ውስጥ ቆይተው ያለ በቂ ዝግጅት የተፈተኑ ተማሪዎች የተለየ ፍትሐዊ ውሳኔ ይፈልጋሉ ብለዋል። በሀገር በተቃጣ ጦርነት የአማራ ክልል ተማሪዎች ተለይው ሰላባ መሆን የለባቸውምም ብለዋል። እንዲህ አይነት ችግር በየትኛውም አካበቢ ይፈጠር ለፍትሐዊነት እንታገላለን ነው ያሉት። ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ዓይናችን ከጉዳዩ ላይ አናነሳም፣ የተወከልነው የሕዝብ ጥያቄ ለመመስ ነው፣ ሌላ ጉዳይ የለንም፣ መተማመን ሊኖረን ይገባል፣ እኛ የሕዝባችን ልጆች ነንም ብለዋል ዶክተር ማተብ። በትምህርት ሚኒስቴር በኩልም በአጭር ጊዜ ውጤቱን ይገልጻል ብለዋል።

አሁን የተፈጠረው እንዲፈታ ጥሩ ሂደቶች መኖራቸውን ያነሱት ዶክተር ማተብ ቀጣይ ተፈታኞች ተገቢ ዝግጅት እንዲያደርጉ የሞራልም የሙያም ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። አሁን ባለው ችግር ተቸክሎ መቆዘምና በችግር መኖር መሸነፍና ተጨማሪ ችግር መፍጠር ነውም ብለዋል። ቀጣይ ተፈታኝ ተማሪዎች በቂ ዝግጅት በማድረግ ታሪክ እንዲሰሩ አደራ ብለዋል። ቢሮውም በማንኛውም ጉዳይ ከተማሪዎች ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል። በተማሪዎች ጉዳይ መቀለድ በሀገር ግንባታ ጉዳይ መቀለድ በመሆኑ በትኩረት እንሠራለንም ብለዋል።

የትኛውም የክልሉ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ በመረጃና በማስረጃ ላይ የተደገፈ ትግል ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። መረጃው የአሚኮ ነው።

Exit mobile version