ETHIO12.COM

ትህነግ 1025 ተሽከርካሪዎችን አልመለሰም፤ 74 ተሽከርካሪ ተጨማሪ እርዳታ ለትግራይ ተላከ

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር / ትህነግ ለትግራይ ሕዝብ የእርዳታ እህልና የህክምና ቁሳቁስ ጭነው የገቡ አንድ ሺህ ሃያ አምስት ከባድ የጭነት ማጓጓዣ ተሽከረካሪዎችን እንዳልመለሰ መንግስት ለዓለም ዓቀፍ ተቋማት አቤቱታ አሰማ። ይህ የተሰማው በሶስተኛው ዙር በትናትናው ዕለት ሰባ አራት ተጨማሪ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በአባአላ መንገድ በኩል ወደ መቀሌ ከተማ እየተጓዙ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሲያስታውቅ ነው።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እንዳለው የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ የገባውን ቃል በማክበር ምቹ የሰብዓዊ ርዳታ ማጓጓዣ ሁኔታን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል።

በዚህም መሠረት በሶስተኛው ዙር ሰባ አራት እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በአባአላ መንገድ በኩል ወደ ትግራይ ክልል መቀሌ ተንቀሳቅሰዋል። ከእነዚህ ውስጥ 6 ተሽከርካሪዎች ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ናቸው።

መንግስት ከዓለም የምግብ ፕሮግራም እና ሌሎችም አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ እንዲደርስ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ይፋ አድርጓል። አክሎም በትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር በኩል ቀናነት እየታየ እንዳልሆነ አስታውቋል።


«አጋር ጅርጅቶች ለትግራይ የሚያቀርቡት የህክምና ቁሳቁስ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ አለባቸው»

እንደ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ያሉ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች የሚያሰራጩት መረጃ መሰረት ቢስ ነው፣

ለትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁስ እያቀረቡ ያሉ አጋሮች የሚያቀርቡት ቁሳቁስ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ እንዳለባቸው የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ገለጹ።


የኢትዮጵያ መንግስት በአስቸጋሪ ሁኔታ ወስጥ የሚገኙት የክልሉ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ወራሪው ሃይል አሁንም ከያዛቸው የአፋርና አማራ ክልል አካባቢዎች እንዲወጣና ምቹ የእርዳታ ማስተላለፊያ መስመርን መዘርጋት እንዲቻል የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግ ጥሪ ያቀረበው መግለጫ፣ ትህነግ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች የሚለቅ ካልሆነ በቀጣይ ምን ሊሆን እንደሚችል አላስታወቀም።

በአፋር የትግራይ ነጻ አውጪ ታጣቂዎች ወረው የያዙትን አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ለቀው ሊወጡ እንደሚችሉ፣ ይህም የሚሆነው እርዳታው ሙሉ በሙሉ ያለገደብ እንዲተላለፍ ሲደረገና በትግራይ አስፈላጊ አገለግሎቶች ሲጅመሩ እንደሆነ ሰሞኑንን ማስታወቁ አይዘነጋም። መንግስት በዚህ ጉዳይ ቀጥታ ምላሽ ባይሰጥም የትግራይ ህዝብ ከችግር ይላቀቅ ዘነድ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

በተጨማሪም ወራሪው ሃይል ከሚነዘቸው የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች እንዲቆጠብ እና እስከአሁን ድረስ ያልተመለሱ 1ሺህ 25 ተሽከርካሪዎች በፍጥነት እንዲመለሱ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግ መንግስት ጥሪ ያቀረበው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ማሳሰቢያን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለጊዜው ያሉት ነገር የለም።

የትህነግ መሪ ዶክተር ደብረጽዮን ሰሞኑንን ለተባበሩት መንግስታት ደርጅት ዋና ጸሃፊ ላኩት በተባለው ደብዳቤ ታጣቂዎቻቸው ዳግም ወደ መሓል አገር የሚያመሩበት አጋታሚ ሊፈጠር እንደሚችል ገልጸዋል። እሳቸው ይህን ቢሉም የኢትዮጵያ መከላከያ ከፍተኛ አዛዦች በተደጋጋሚ ሲሉ እንደሚሰማው መከላከያ ክንዱን ማጠንከሩ፣ ለማንኛውም ግዳጅ ዝግጁ መሆኑና እጅግ ዘማናዊ ትጥቅ መላበሱ፣ አየር ሃይሉና የምድር ሃይሉ በጥምረት ዘመቻ ማካሄድ የሚችሉበት ደረጃ ከፍተኛ በመሆኑ በየትናውም መመዘኛ ትህነግ ካሁን በሁዋላ ስጋት ሊሆን እንደማይችል ነው።

ትህነግ በከፈተና ደረጃ ወታደራዊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንን የሚያመላክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው። ከዚያ አካባቢ የመጡና ለመንግስት እጅ የሰጡ እንዳሉት በትግራይ አፈሳና የግዳጅ ምልመላ በመላው ክልሉ ይካሄዳል። አርአያ በፕሮግራሙ ያቀረባቸው ሃይደር ሆስፒታል የሰሩ የነበሩና በቅርቡ ለመንግስት እጃቸውን የሰጡ የህክምና ባለሙያ እንዳሉት በትግራይ ሕዝቡ ከፍተኛ ስቃይና ችግር ውስጥ ነው። በግድ ልጆች እየተመለመሉ ሲሆን ልጁን የደበቀ ይቀጣል።

የትህነግ ታጣቂዎች የመዋጋት ፍላጎትና ሞራል እንደሌላቸው፣ የሚናገሩ እንደሚሉት በትግራይ አሁን ለዳግም ጦርነት ወስኖ መነሳት ተቀባይነት ስለሌለው የተጀመረውን የሰላም አካሄድ አጠናክሮ መያዝ አማራጭ የለውም።

በአፋር ክልል ብቻ ሳይሆን በአማራ ክልል ትህነግ ወሮ ከያዛቸው አካባቢዎች መካከል የዋግ ወረዳዎች ይጠቀሳሉ። ዓርብ ዕለት ሕዝብ ያነጋገሩት ጠ/ሚኒስትር አብይ በወረራ የተያዙት አካባቢዎች ነጻ እንዲወጡላቸው መጠያቃቸውን የመንግስት የዜና አውታሮች አመልክተዋል። ቀደም ሲልም ሕዝቡ ከመከላከያ ጎን ለመቆም መዘጋጀቱን ጠቅሶ በወረራ የተያዙት አካባቢዎች ነጻ እንዲወጡ ጥያቄ ማቅረቡን ውይይቱን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።

የትግራይ፣ የአፋርና የአማራ ሕዝብ በፖለቲካ ሴራና የልጣን ሽኩቻ ለዚህ ሁሉ ችግር መዳረጉ እጅግ እንደሚያሳዝናቸው የሚናገሩ “ጦርነት እንዲቆም ጫና እንፍጠር” ሲሉ፣ ዓላማቸውና ፍላጎታቸው በውል ያልተቀመጠ ተከፋይ ሚዲያዎችና “ተላላኪ” የሚባሉ አክቲቪስቶች እሳት እንዲነድ በየቀኑ እያካሄዱ ያሉት ዘመቻና የጥላቻ ቅስቀሳ ስጋት እንደሆነባቸው የሚናገሩም በርካታ ናቸው።

Exit mobile version