Site icon ETHIO12.COM

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ገለጹ

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲኾኑ ኮሚሽኑ በቀጣይ በሚያካሂዳቸው ተግባራት ላይ እገዛ በማድረግ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ገለጹ።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እስካሁን የሄደበትን ርቀትና ቀጣይ ተግባራት በተመለከተ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤና ከኮሚሽኑ አባላት ጋር ውይይት አካሂደዋል።

በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መኾኑን ይደነግጋል።

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የኮሚሽኑን የእስካሁኑን ሂደት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር) በተለይም የምክክር ኮሚሽን አዋጁን አዘገጃጀት ሂደት በተመለከተ ሰፋ ያለ ገለጻ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኮሚሽኑ መቋቋሚያ አዋጁ ሲፀድቅ በተቻለ መጠን የኹሉንም የባለድርሻ አካላት ድምጽ እንዲካተት መደረጉን ያስታወሱት ሚኒስትሩ ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ፓርቲዎቹ ባደረጉት ተሳትፎም የመቋቋሚያ አዋጁ የታለመለትን ግብ እንዲመታ በተለይም ገለልተኛና ኹሉን አቀፍ ለማድረግ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ጠቁመው የፓርቲዎቹ ሐሳብ በግብዓትነት መካተቱን ተናግረዋል።

አዋጁ እስካሁን የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማቋቋም ከወጡት አዋጆች በአንጻራዊነት የተሻለ ነጻነትና ገለልተኝነቱ የተረጋገጠለት አዋጅ መኾኑን ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክሩ በአንዳንድ የፖለቲካና የሐሳብ መሪዎች እንዲሁም በአንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር መኾኑን ጠቁመዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት ሲንከባለል የቆየውን የፖለቲካ ጥያቄ መፍትሔ ለመስጠት መንግሥትም ኀላፊነቱን ወስዶ ወደ ሥራ ማስገባቱን አድንቀው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎም የሚበረታታ መኾኑን ነው ያነሱት።

ይህም ኾኖ በምክክር የዝግጅት ምዕራፉ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ የተፈለገውን ያህል አለመኾኑን አንስተዋል። በቀጣይ ኮሚሽኑ በሚያካሂዳቸው ተግባራት ላይ ፓርቲዎች የላቀ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መሥራት ይገባል ብለዋል።

በተለይም ሂደቱ ለሕዝቡ ግልጽና ተዓማኒ እንዲኾን የሚያስችሉ አሠራሮችን መዘርጋት እንደሚገባ ተናግረዋል። የኮሚሽኑ ወሳኝ ተግባራት በመገናኛ ብዙኀን ሽፋን ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

ኮሚሽኑም ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ተጽዕኖ ነጻ ኾኖ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ቀጣይ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና ምክክሩ ግቡን እንዲመታ ያላቸውን ዝግጁነትም ገልጸዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፥ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስኬታማ እንዲኾን የኹሉም ሚና ወሳኝ መኾኑን ጠቁመዋል። በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሊኾን ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለዚህም ኮሚሽኑ ከፓርቲዎቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችለውን ሥራ እያከናወነ መኾኑን አመላክተዋል።

ፓርቲዎች ኢትዮጵያ በታሪኳ የምታካሂደው ትልቅ ኹነትና ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የፖለቲካ ሥርዐት የሚያሸጋግራት የምክክር ኮሚሽን ስኬታማ እንዲኾን የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው በምክክር ኮሚሽኑና በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርና የኮሚሽኑን ቀጣይ ሂደቶች ስኬታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 55 (1) መሠረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራዎቹን በአራት ምዕራፍ ከፍሎ እያከናወነ መኾኑን ገልጿል።

Exit mobile version