Site icon ETHIO12.COM

በአፍሪካ ቀንድ የመረጃ ልውውጥን በማሳለጥ የጋራ ግንኙነትን ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተካሄደ

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር፣ የዲ.ሲ.አይ.ኤስ (International Security Cooperation Directorate (DCIS)) ትብብር ቢሮ ኃላፊ ጂን ክሪስቶፍ ሂላሪ እና በኬኒያ የዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት ኢንተርፖል (Interpol) ኃላፊ ጌዲዮን ኪሚሉ ጋር ተወያይተዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በተለይም በህገ-ወጥ ሰዎች ዝውውር ወንጀል ላይ የሚሳተፉ ቡድኖችን የግንኙነት መረብ ለመበጣጠስ እንዲያስችል በአፍሪካ ቀንድ የህግ አስከባሪ አካላት መካከል የመረጃ ልውውጥን በማሳለጥ የጋራ ግንኙነትን ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል።

ልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ስራ በተለይም በሲሲቲቪ ካሜራና የፖሊስ ድጂታል መገናኛ ራዲዮ እንዲሁም አለም አቀፍ ስታንዳርድ ጠብቆና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ ሰብዓዊ መብትን ባከበረ መልኩ እየተሰራ ያለውን የወንጀል ምርመራ አሰራር ጎብኝተዋል፡፡

ልዑኩ በፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር የሲቪፖል ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አን-ሶፊ ሳንዶርና በፈረንሳይ የሮክ ቴክኒካል ዳይሬክተር ፊሊፕ ክሬስፖ እንዲሁም የፕሮጀክቱ ቀጠናዊ አስተባባሪ ሙክታር ረመዳን እና ሌሎች አባላትን ያካተተ ነው።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል፣ ከሮክና ሲቪ ፖል ጋር በመተባበር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም በወንጀል ድርጊት ተፈላጊዎችን ለፍትህ ለማቅረብ በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የተጀመሩ የጋራ ኦፕሬሽኖችን የምርመራ ስራዎችን አጠናክሮ የማስቀጠል ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

ጂን ክሪስቶፍ ሂላሪ በበኩላቸው፣ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር የተሰሩ ኦፕሬሽኖች ውጤታማ በመሆናቸው ግንኙነታችንን ወደ ፊት በበለጠ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

ሚስተር ጌዲዮን ኪሚሉ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ምስራቅ አፍሪካን ከወንጀል ነፃ ቀጠና ለማድረግ በግዳጅ ላይ ለተሰማሩ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መኮንኖችና አባላት በዲጅታል የፖሊስ መገናኛ ራዲዮ ምስጋና በቀጥታ አቅርበዋል፡፡ ተቋሙ በጠንካራ አመራር እየተመራ መሆኑን ተረድቻለው ያሉት ኃላፊ የሀገሪቱን የቀጠናውን ሰላም ለማረጋገጥ ጠንክራችሁ እንደምትሰሩ እተማመናለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀልን ለመከላካልና ለመመርመር እየሰራ ያለው የቴክኖሎጂ ማስፋፋትና የሪፎርም ትግበራ በምስራቅ አፍሪካ ዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅትም (Interpol) መተግበር ያለበት መልካም ተሞክሮ መሆኑን ገልፀው ለቀጠናው የፖሊስ ተቋማት ጭምር ሞዴል እንደሚሆን በአድናቆት ገልፀዋል። በቀጣይም ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በቅርበት ቢሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑም አረጋግጠዋል። via ENa

Exit mobile version