ኢትዮጵያና ቻይና በጋራ ትብብር የተሰሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ደህንነት ጥበቃን ለማጠናከር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

ኢትዮጵያ እና ቻይና በጋራ ትብብር የተሰሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ደህንነት ጥበቃን ለማጠናከር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ። የመግባቢያ ሰነዱን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩአንና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ተፈራርመዋል። ሚሽነር ጀነራል ደመላሽ የሁለቱ ሀገራት የቆየ የባህል፣የታሪክ፣የስልጣኔ ግንኙነቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖለቲካና በኢኮኖሚ መስክ እየተጠናከረና እየዳበረ መምጣቱን ገልፀዋል።

እንዲሁም ቻይና በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ቀዳሚ ሀገር መሆኗን በማንሳት ዛሬ የተደረገዉ ስምምነትም የሁለቱን ሀገራት የቆየ አጋርነት በማጠናከር፤በጋራ ለመልማትና ለመበልፀግ ቅድሚያ መስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራሉ አክለውም ተቋሙ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ሪፎርም እያካሄደ ባለው በዚህ ወሳኝ ወቅት በአፍሪካ ካሉ ምርጥ አምስት የፖሊስ ተቋማት ውስጥ የሚመደብና ሙያዊ ብቃትን ያረጋገጠ አካታች እና በህዝብ ታማኝ የሆነ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት ለመፍጠር እሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቻይና መንግስት ያደረገዉ የሎጂስቲክስ ድጋፍ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አንስተዉ የተደረገዉ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ፊርማም ተቋሙ የነደፈዉን ራእይ እንዲሳካ በማድረግ የጎላ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያሉ በቻይናዉያን የሚገነቡ፣ተገንብተዉ ያለቁና አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች ደህንነታቸዉ እንዲጠበቅ በማድረግ በኩልም ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ሀላፊነት ወስዶ እንደሚሰራ ኮሚሽነር ጀነራሉ ቃል ገብተዉላቸዋል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱ ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በኢትዮጵያ እና በቻይና የጋራ ትብብር የተሰሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ደህንነት በተጠናከረ መልኩ ለመጠበቅና የሁለትዮሽ ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር መሆኑ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ አንድ ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የዋጋ ግምት ያላቸው በርካታ የደህንነት መሣሪያዎችን ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በድጋፍ ሰጥቷል፡፡

ቁሳቁሶቹ የባቡር መንገዱ ተሳፋሪዎች የደህንነት ፍተሻ የሚያገለግሉ አምስት ኤክስሬይ የመፈተሽያ መሳሪያዎች፣55 በእጅ የሚያዙና አምስት ተንቀሳቃሽ የብረት መፈተሽያዎች ሲሆኑ የባቡር መስመሩን የደህንነት ጥበቃን ለማሻሻል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ መግለፃቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ቻይና እና ኢትዮጵያ ጠንካራ የንግድ እና የኢኮኖሚ ትስስር ያላቸው መሆኑን የገለፁት አምባሳደሩ ቻይና የኢትዮጵያ ትልቁ የንግድ እና የኢንቬስትመንት አጋር እንዲሁም የትላልቅ ፕሮጄክቶች ኮንትራክተር ሆና እየሰራችና የቻይና ካምፓኒዎች ከ1 ሺህ 600 በላይ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

See also  የመረጃ ሙያተኞች በመረጃ ሙያ ዐይንና ጆሮ ሁኑ

Leave a Reply