Site icon ETHIO12.COM

ከደሴ ከተማ ቤተ-እምነቶች እና ህዝባዊ ተቋማት ህብረት የተሰጠ መግለጫ

በጎንደር ከተማ ስለተፈጸመው ክብር የሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት መዝረፍ በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በጎንደር ከተማ በተፈጸመው ክብር የሰው ልጆች ግድያ የመስጊድ ቃጠሎ እና ንብረት መዘረፍ ዜና ስንሰማ ከፍተኛ ሀዘን ተስምቶናል፡፡

ሁሉም ሀይማኖት የሰላም ምክንያት እንጅ የመገዳደል ምክንያት ይሆናል ብለን አናምንም፡፡ ሀይማኖት ሽፋን አድርገው እርስ በርሳችን እንድንጣፋ የሚሰሩ ስውር ዓይን ያላቸው ሰዎች የፈጸሙት ክፍ ድርጊት ሊሆን እንደሚችል እንገምታለን፡፡

ጻድቅ እንኳን ለክብር የሰው ልጅ ህይወት ይቅርና ለእንስሳት ሕይወት እንደሚራራ ቅዱሳን መጽሀፍት አስተምሮናል፡፡

ስለሆነም ፡-

1. በጎንደር ከተማ በተፈጸመው ክብር የሰው ልጆች ግድያ የመስጊድ ቃጠሎና የንብረት መዘረፍ ማንኛውም የእምነት ተቋም የማይወክል ስለሆነ ከልብ እናወግዛለን፡፡

2.ጉዳቱ የደረሰባችሁ ሁሉም ወገኖቻችን መጽናናትና ጽናት እንዲሆንላችሁ የጸለይን ህመማችሁ ህመማችን እንደሆነ ከልብ እናረጋግጥላችኋለን፡፡

3.ሙስሊም ወገኖቻችን መጭው ኢድ አልፈጥር በአል በጽናትና በፈጣሪ ትእግስት በርትታችሁ በሰላማዊ መንገድ እንድታከብሩ እየተመኘን ለኢድ አችሁ መሳካት ከጎናችሁ የምንቆም መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

4.በእምነት ተቋሞቻችን ውስጥ ተሰውራችሁ የጥፉት አጀናዳችሁን የምትፈጽሙ አካላት የተሰወረውን የሚያይ ፈጣሪ ይፈርዳልና በአስቸኳይ እጃችሁን እንድትሰበስቡ በጥብቅ እንጠይቃለን፡፡

5. ወላጆች ለየቤተእምነታችን እና ለሀገራችን እድገት የሚያስፈልጉትን ወጣት ልጆቻችንን በእኩይ አላማ ተታለው የራሳቸውና የየቤተእምነታቸውን ህልውና አደጋ ላይ እንዳይጥሉ እንድትመክሩና እንድትጠብቁ አደራ እንላለን፡፡

6.የመንግስት አካላትም በእምነት ሽፋን የጥፋት ሴራ የሚሰሩትን ቤተእምነቶቻችንን ስለማይወክሉ ወንጀለኛን የመቆጣጠር ወጀልን የመከላከል ሀላፊነታችሁን በጊዜው እንድትወጡ እንጠይቃለን፡፡

7. በሁሉም ሀገራችን ክፍሎች ያላችሁ የሁሉም እምነት ተከታዮች ችግሮችን ሀይማኖታዊ እሴታችንን በጠበቀና በሰላማዊ መንገድ መፍታት ባህላችሁ እንድታደርጉና በሌሎች አካባቢ ችግሩን በማስፋት ተጨማሪ ጉዳት ሊያደርስብን ከሚችል ማንኛውም የሀይል እርምጃ ሁሉ እንዲታቀቡ በፈጣሪ ስም አደራ እንላችኋለን፡፡

ሚያዚያ 21/2014 ዓ.ም

የደሴ ከተማ ቤተእምነቶችና ህዝባዊ ተቋማት ህብረት

የህብረቱ አባላት ፦

የደሴ ከተማ የሁሉም ቤተእምነቶች

የደሴ ከተማ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት

የደሴ ከተማ ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት

የደሴ ከተማ ነጋዴ ሴቶች ማህበር

የደሴ ከተማ መምህራን ማህበር

የደሴ ከተማ አቀፍ እድሮች

አብዱልከሪም ሙስጠፋ

Exit mobile version