Site icon ETHIO12.COM

በሃይማኖትን ሽፋን የሚፈጸሙ የወንጀል ተግባራትን መንግሥት እንዲያስቆም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠየቀ

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በወራቤ ከተማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት እና በፕሮቴስታንት አማኞች ቤተ አምልኮዎች ላይ የተፈፀውን ጥቃት በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት እና በፕሮቴስታንት አማኞች ቤተ አምልኮዎች ላይ የተፈፀውን ሕገ ወጥና የወንጀል ተግባር በእጅጉ እንደሚያወግዝ ገልጿል፡፡

ተግባሩ በየትኛውም ሃይማኖት ተቀባይነት የሌለው ከሆኑም በላይ ደረቅ ወንጀልና በህግ ሊያስጠይቅ የሚገባው ተግባር መሆኑንም ጉባኤያችን በጽኑ ያምናል ነው ያለው፡፡

ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ የተፈፀመውን አስነዋሪ ተግባርን አስመልክቶ ጉባኤያችን በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ ተግባሩን አምርሮ በማውገዝ ጥፋትን በጥፋት፣
ወንጀልን በወንጀል ለማረም የሚደረግ ሙከራ እንዳይኖር ማስገንዘባችን ይታወሳል በማለት አብራርቷል፡፡

ይሁን እንጅ ትናንት በሆነው ሁሉ አዝነን ሳንጨርስ ይህ መከሠቱ በእጅጉ አሳዝኖናል ሲል ገልጿል፡፡

ሁሉም ሃይማኖቶች ሰላምን የሚሰብኩ፣ትምህርትን የሚያስተምሩና ለሌሎች ስለመኖርና መስዋዕት ስለመክፈል የሚገዳቸው እንደሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም በሃይማኖት ስምና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚፈጸመው ሕገ ወጥነትና ወንጀል እንደሆነ ታውቆ መንግስት ሕግና ስርኣትን እንዲያስጠበቅ ጉባኤያችን አበክሮ ይጠይቃል ብሏል።

መንግስት ሕግና ስርኣትን ለማስፈፀም እንዲችል ቀደም ብሎ ያወጣቸውን ህጎችን ሁሉ ተፈፃሚ ሊያደርግ ይገባል ነው ያለው መግለጫው፡፡

ሕዝበ ሙስሊሙም ይሁን ሕዝበ ክርስቲያኑ ችግሮች እንዳይባባሱም አንዱ ሌላውን በመጠበቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ እየጠየቅን ችግር ፈጣሪዎችንም በማጋለጥና አሳልፎ ለሕግ አካላት መስጠት እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን ብሏል፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያው መልዕክት የሚላላኩ አካላትም በምትጽፉት ጽሁፍና በምታስተላልፉት መልዕክት ሀገራችሁንና ወገናችሁን ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጥ ሁሉንም ተግባር በማስተዋል እንድትከውኑ እየጠየቅን በሃይማኖት ስም የሚደረግ ጥላቻ ቅስቀሳን ባለማጋራት ኃላፊነታችሁን እንዲወጡ አደራ እንላለን ብሏል፡፡ via ENA

Exit mobile version