Site icon ETHIO12.COM

መከላከያ ሚኒስቴር ለዜጎች ደኅንነት ስለቀየሰው ስትራቴጂ ማብራሪያ ተጠየቀ

የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የዜጎችን የደኅንነት ስጋት ለማስቀረት የቀየሰው ስትራቴጂ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተጠየቀ።

ቋሚ ኮሚቴው የተቋሙን የ9 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ሰሞኑን ስገመግም ነው ማብራሪያ እንዲሰጥ የጠየቀው።

ለሀገሪቱ ሰላምና ደኅንነት የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ያለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በኅብረተሰቡ ዘንድ የኅልውና እና የአጠቃላይ ደኅንነት ስጋት የሚፈጥሩ በየቦታው የሚነሱ ግጭቶችን ለማስቀረት ምን ስትራቴጂ ቀይሶ እየሠራ እንደሚገኝ ኮሚቴው ጠይቋል።

ኮሚቴው አክሎም ሕገ-ወጥ ታጣቂዎችን አደብ ከማስገዛት አንጻር፣ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት የተሠውትን የመከላከያ ሰማዕታት ቤተሰቦች በዘላቂነት ከመደገፍና የአባላቱ ደመወዝ እና ቀለብ ከኑሮ ውድነቱ ጋር እንዲጣጣም ስለሚሠሩት ሥራዎች ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ከእነዚህም ባሻገር በየትኛውም ወታደራዊ ግዳጅ ላይ ለሌሉ አባላት ደመወዝ እየተከፈለ መሆኑ እና ክልሎች የራሳቸውን ልዩ ኃይሎች የማደራጀት ተግዳሮት ጉዳይ በተቋሙ እንዴት ይታያል የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል።

ሪፖርቱን ያቀረቡት የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ 7 ዋና ዋና ግቦችን ይዞ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።

ከእነዚህም ሕገ-መንግሥቱን ማስከበር፣ ሕዝብን እና ሀገርን ከውስጥ እና ከውጭ ጠላት እና ወራሪ መከላከል፣ ሀገራዊ ወታደራዊ ዓቅምን ማሳደግ እንዲሁም ተቀማዊ ለውጥን እና ዕድገትን ማረጋገጥ የሚሉት ግንባር-ቀደም ናቸው ማለታቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። via – (ዋልታ)

Exit mobile version