Site icon ETHIO12.COM

ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አካባቢ በርካታ የፀጥታ ኃይል አሰማራች

ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው የማርሳቢት ግዛቷ ውስጥ በተቀሰቀሰ የጎሳ ግጭት ምክንያት በርካታ ሰዎች መገዳላቸውን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች እና የፀጥታ ኃይሎች መሰማራታቸው ተገለጸ።

በማርሳቢት ለተፈጠረው የፀጥታ ችግር መንስኤ ድርቅ፣ ፖለቲካዊ ቅስቀሳ እና በግጭት ከምትታመሰው ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ በቀላሉ መገኘቱ ነው ሲል መንግሥት ገልጿል።

የኬንያ የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ፖሊስ ከደቡብ ኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ የገቡ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን እና ጥይቶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተናግረዋል።

የኬንያ መንግሥት በማርሳቢት የፀጥታ ኃይል ከማሰማራት በተጨማሪ ለአንድ ወር የሚቆይ የሰዓት እላፊ አዋጅ እንዲሁም ትጥቅ እንደሚያስፈታም ገልጿል።

በማርሳቢት ከተማ በቅርቡ የተፈጸመውን ግድያ አረመኔያዊ ሲል የኬንያ መንግሥት ያወገዘው ሲሆን በዚህም የአካባቢው አስተዳዳሪም ተገድለዋል።

በአፍሪካ ቀንድ በድርቅ ክፉኛ ከተጎዱ አካባቢዎች አንዱ በሆነው የዚህ ድንበር አካባቢ ከብት ዘረፋም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

ከመንግሥት ወታደሮች ጋር በጦርነት ውስጥ ያለውና አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የስልጠና ሜዳዎች በኬንያ ያለው ሲሆን በኬንያ ከሚገኘው የኦሮሞ ማኅበረሰብም የተወሰነ ድጋፍ አለው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

Exit mobile version