Site icon ETHIO12.COM

«የትግራይ ሕዝብ ያተረፈው መከራና ስቃይ ነው»

“አሸባሪው ህወሓት የሚፈፅምብንን ግፍ ከቀዬአችን አፈናቅሎናል” – የትግራይ ክልል ነዋሪዎች

አሸባሪው ህወሓት የሚፈፅምብን ግፍና መከራ ከቀዬአችን አፈናቅሎናል ሲሉ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በአማራ ክልል በሃይቅ ጃሬ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን የአማራ ክልል ሕዝብ በሚችለው ሁሉ ወገናዊ ድጋፍ እያደረገላቸው መኾኑን ገተናግረዋል።

“ከቀዬአችን ተፈናቅለን ወደ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መጥተናል፣ ሕዝቡም ተቀብሎ እያስተናገደን ነው” ብለዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን የአማራን ሕዝብ ጠላት አድርጎ ጥላቻ ቢሰብክም ህዝቡ በፍቅር ተቀብሎ እያስተናገዳቸው እንደኾነ ተናግረዋል።

ጠላታቸው የአማራ ህዝብ ሳይሆን ለስልጣን ጥሙ ግፍና መከራ የሚፈጽምባቸው ህወሃት እንደኾነም ገልጸዋል።

ቡድኑ ከስምንት ወራት በላይ አስሮ ያሰቃያቸው ከመቀሌ ከተማ የተፈናቀሉት አቶ ጌትነት ስመኘው ለኢዜአ እንደገለፁት፤ አሸባሪው ህወሀት እታገልለታለሁ ለሚለው የትግራይ ሕዝብ ያተረፈው መከራና ስቃይ ነው።
ህወሀት ሕዝቡን ገንዘብ አምጣ፣ እህል አዋጣና የሚዋጋ ልጅ ስጥ እያለ የሚያሰቃይ መኾኑን ገልጸው፤ የቡድኑን ፍላጎት ማሟላት ያልቻለ ለእስርና ለእንግልት ብሎም ለሞት እንደሚዳረግ ተናግረዋል።

ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በብዙ መከራ አማራ ክልል በመግባታቸው በመንግሥትና በኅብረተሰቡ ድጋፍ የዕለት ደራሽ ምግብ፣ አልባሳትና የተለያየ ቁሳቁስ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ከአሸባሪው ቡድን ጭቆና ነጻ መውጣታቸው እፎይታ እንደሰጣቸውም ተናግረዋል።

ከመሆኒ ከተማ የተፈናቀለው ወጣት ጀማል መሐመድ እንዳለው የትግራይ ህዝብ የአሸባሪውን ህወሓት ስውር ደባ ተገንዝቦ ከኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን የሽብር ቡድኑን ማጥፋት አለበት።

”ቡድኑ ለሕዝቡ የሚመጣውን የእርዳታ እህል ለትግራይ ልዩ ኃይልና ለአመራሩ ቤተሰብ ከመስጠቱ በላይ ሕዝቡን ሀገር የማፍረስ ሴራውን ለማስፈፀም ገንዝብና ቁሳቁስ አምጡ እያለ መቆሚያና መቀመጫ አሳጥቶታል” ሲል ተናግሯል።

ወጣት ጀማል አሸባሪው ቡድን ለጦርነት ሊማግደው እንደነበር ገልጾ፤ አልዘምትም በማለቱ ለእስር መዳረጉንና አምስት ሺህ ብር ቅጣት መክፈሉን አንስቷል።

አሸባሪው ህወሀት የሚለውና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃሳብ ፈጽሞ የማይገናኝ መኾኑን የትግራይ ሕዝብ ተገንዝቦ የሽብር ቡድኑን በቃህ ብሎት በጋራ አምርሮ መታገል እንዳለበትም አስገንዝቧል።

የሽብር ቡድኑ በሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና መከራ የሴቶችን ህይወት አመሰቃቅሏል፤ ወላድ እናቶችን ያለ ልጅ አስቀርቷል፣ ንብረታችንን ዘርፏል ያሉት ደግሞ ከአላማጣ ከተማ የመጡት ወይዘሮ ፈንታነሽ ኀይሉ ናቸው፡፡

ከቀያቸው ተፈናቅለው አማራ ክልል በመግባታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ እርስ በርሳችን የተጋባንና የተዋለድን የማንለያይ ሕዝቦች በመኾናችን በደስታ ተቀብለው በማስተናገድ እንደማንለያይ በተግባር አሳይተውናል ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ እንዲጠፋና በኢትዮጵያ አስተማማኝ ዘላቂ ሰላምና አንድነት እንዲመጣ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኀላፊ አቶ ኢብራሂም ይመር በበኩላቸው ወደ አማራ ክልል የሚገቡ የትግራይ ክልል ተፈናቃይ ወገኖች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን የተጠለሉ በርካታ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በደቡብ ወሎም ሐይቅ ጃሬ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ከ640 በላይ የትግራይ ተፈናቃይ ወገኖች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

የአማራና የትግራይ ሕዝብም ላይለያይ በብዙ ነገሮች የተሳሰረ በመኾኑ ተቀብሎ እየተንከባከባቸው መኾኑን ተናግረዋል።

መንግሥት ኅብረተሰቡን በማስተባበር የዕለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ እያቀረበ ሲሆን ህወሀትና የትግራይ ሕዝብ አንድ አለመሆኑን በተፈናቃዮች ማረጋገጥ እንደሚቻል ገልፀዋል።

የሁላችንም ጠላት አሸባሪው ህወሀትና ግብረ አብሮቹ በመሆናቸው ቡድኑ ከነክፉ ሃሳቡ እንዲወገድ በጋራ መታገል ይገባል ብለዋል።

Exit mobile version