Site icon ETHIO12.COM

አብን አስር አመራሮቹን አገደ-ክርስቲያን ታደለ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከድርጅት ህገ-ደንብና አሰራር ውጭ በመሆን አፍራሽ ድርጊቶችንና የዲሲፕሊን ጥሰቶችን በፈፀሙ አስር ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮችን አገደ። ” ልክ ይሁንም፥ አይሁንም መሰል ውሳኔዎችን ለመወሰን ግን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሥልጣን የሌለው መሆኑን ለንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች መግለጽ እፈልጋለሁ” ሲሉ አቶ ክርስቲያን በብዛት በሚሳተፉበት የፌስ ቡክ ገጻቸው ጽፈዋል።

“ለሚመለከተው ሁሉ” ሁሉ ብለው ባሰራጩት አጭር ጽሁፍ አቶ ክርስቲያን ” ንቅናቄው የተመሰረተባቸውን ሕዝባዊና አገራዊ ጥያቄዎች ከግብ እንዲያደርስ ሁላችንም በጎ ሚና እንድንጫዎት አደራ ማለት እፈልጋለሁ” ብለዋል። እሳቸው ይህን ቢሉም ንቅናቄው “የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በ29/08/2014 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በፓርቲው መዋቅር የተለያዩ የሃላፊነት እርከኖች ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ የዲሲፕሊን እና ድርጅታዊ መርህ ጥሰቶችን በተመለከተ በጥልቀት ተወያይቶ የድርጅቱን መተዳደሪያ ደንብ የተለያዩ ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል” ሲል በህገ ደንቡ መሰረት አቶ ክርስቲያንን ጨምሮ የተወሰነው ውሳኔ ደንብን የተከተለ ስለመሆኑ አስታውቋል።

አቶ ክርስቲያን ከንቅናቄው አመራሮች በተለየ መልኩ ቅኔ፣ የክተት ጥሪ፣ የተነሱ መልዕክት በተደጋጋሚ ሲያሰራጩ የሚመለከቱ፣ ውጭ ካሉ ሚዲያዎችና በአገር ውስጥ ካሉ አንድንድ ሚሊሻ በማደራጀት ስማቸው ከሚነሳ ሃይሎች ጋር ተናበው እንደሚሰሩ ሲናገሩ ነበር። ንቅናቄያቸው እንዴት ዝም እንዳላቸው ሲጠይቁ የነበሩ ” አቶ ክርስቲያን ያለመከሰስ መብታቸው ሊነሳ ይገባል” ሲሉ ሲከራከሩም ነበር።

” ንቅናቄው የተመሰረተባቸውን ሕዝባዊና አገራዊ ጥያቄዎች ከግብ እንዲያደርስ ሁላችንም በጎ ሚና እንድንጫዎት አደራ ማለት እፈልጋለሁ” ሲሉ በፌስ ቡክ ገጻቸው ያስታወቁት አቶ ክርስቲያን ንቅናቄው ባወጣው መግለጫ ላይ “… ንቅናቄውን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ አንጀኞች ጋር ሕብረት በመፍጠርና ፣ ንቅናቄው የሃሳብና የተግባር አንድነት እንዳይኖረው በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ስተለገኙ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ተወስኗል” ሲል ድርጅቱን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ መሆኑንን ይፋ አስታውቋል።

አቶ ክርስቲያን በጎጃም አካባቢ ድጋፍ ያላቸው ቢሆንም በርካቶች ከአቶ በረከት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸውና በንቅናቄው ውስጥ ካሉት እንደነ አቶ ዩሱፍ፣ ጋሻው መርሻና ሊቀመንበሩ ሚኒስትር በለጠ ሞላ እርጋታ የማይታይባቸው፣ በመልዕክቶቻቸው ሁሉ የማነሳሳትና እንደ ፓርላማ አባል ሃላፊነት የጎደላቸው እንደሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ቅሬታ ቀርቦባቸዋል። በንቅናቄያቸው ውስጥም በተደጋጋሚ በዚሁ ” ፈር የለቀቀና ለመታገል በማይመች አካሄድ ሲገመገሙ ነበር” ሲሉ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ሲናገሩ ነበር።

እሳቸው ቢቃወሙትም ንቅናቄው የሚከተለውን ውሳኔ ከነማብራሪያው አቅርቧል። እንዳለ አትመነዋል።

ሀ. የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው የንቅናቄያችን የስራ አስፈጻሚ አባል በተመለከተ

አቶ ክርስቲያን ታደለ ፀጋዬ የንቅናቄው ከፍተኛ አመራር ሆነው ሳለ ፣ የተጣለባቸውን ከፍተኛ ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው በተለያዩ አፍራሽ ድርጊቶች ላይ የተሳተፉ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሁለት ጊዜ የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም በንቅናቄው ሥራ አስፈፃሚነታቸውም ሆነ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው በጋራ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ተገዥ ባለመሆን እና ንቅናቄውን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ አንጃኞች ጋር ሕብረት በመፍጠርና ፣ ንቅናቄው የሃሳብና የተግባር አንድነት እንዳይኖረው በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ስተለገኙ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ተወስኗል፡፡


Read also this

ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ … “አማራ ወደ አራት ኪሎ አምራ” የተከበሩ አቶ ክርስቲያን አዘዙ .

ከአንድ ድርጅት የተቀዱት አቶ የሱፍና አቶ ጋሻው እንደ ፖለቲካ መሪና አታጋይ እጅግ የበስለ መረጃና ጥንቃቄ የተሞላበት ሃሳብ ሲያሰራጩ፣ በተከበረ ማዕረግ የተጠቀለሉት የጎጃሙ አቶ ክርስቲያን አንድንዴም አጀንዳ አከፋፋይ፣ አጀንዳ ቀርጪና አቅጣጫ አሳይ በመሆን ሚዲያው ምን ላይ ማተኮር እንዳለበት መረጃ ሲያጋሩ ይታያሉ። አንዳንዶች እንደሚሉት አቶ ክርስቲያን ውጭ ካሉ ሃይሎች ጋር ይናበባሉ። ሰሞኑንን ይህን ብለው ነበር …..


ለ. ከድርጅት ማገድ

በፓርቲው መዋቅር ውስጥ በተለያየ የሃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ የንቅናቄው መካከለኛ አመራሮችና አባላት የሆኑት:-

  1. አቶ አንተነህ ስለሺ መርዕድ ፣
  2. አቶ እሱባለው ሙላት ዘለቀ ፣
  3. አቶ ንጉሥ ይልቃል ያለው ፣
  4. አቶ ዓለሙ ወልዴ አከለ ፣
  5. ዶ/ር ጌታሁን ሣህሌ ወልዴ /የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል/ ፣
  6. አቶ የማነ ብርሃን ሙጬ ፣
  7. አቶ ጓዴ ካሴ ወልዴ ፣
  8. አቶ ስንታየሁ ተስፋው ስዩም ፣
  9. አቶ እስክንድር ለማ በቀለ ፣
  10. አቶ ጌታነህ ወርቁ ይርዳው ፣

በድርጅት አመራርነት የተጣለባቸውን ሃላፊነት ወደጎን በመተው በሚከተሉት ህገወጥ ድርጊቶች ተሳታፊና መሪ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
• በፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ ወይም ጠቅላላ ጉባኤ የጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅትን በሚመለከት የተሰጣቸው ውክልና ሳይኖር ፣ የጠቅላላ ጉባኤ ተወካይ ነን በማለት ህገወጥ ቅስቀሳና አድማ መምራትና በንቅናቄው ውስጥ አንጃ መፍጠር ፤
• የጉባኤ አባላትን በተለያዩ አሉባልታዎች በማደናገር እና የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ፊርማ ማሰባሰብ ፣ ህገወጥ የጠቅላላ ጉባኤ ውክልና ይገባኛል መጠየቅና ድርጅታዊ ሥልጣን በእጅ አዙር ለመንጠቅ መሞከር ፤
• ከንቅናቄው እውቅና ውጭ የሆኑ የቴሌግራም ቡድኖችን በመክፈት አፍራሽ ቅስቀሳዎችን ማድረግ ፤
• የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ምንም አይነት ስልጣን ሳይኖራቸው ፣ ጉባኤ ጠርተን ሪፎርም እናካሂዳለን በማለት ከድርጅቱ እውቅና ውጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ፤

• የድርጅትን ደንብ ተላልፎና ከሚመለከተው ክፍል ፈቃድ ሳይኖር በየሚዲያው መግለጫ መስጠት ፣ ድርጅታዊ ምሥጢር ማባከን ፤
• በንቅናቄው ላይ መሰረተ ቢስ ክሶች በመሰንዘር እና በከፍተኛ አመራሩ ላይ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈት ፤
ከባድ ቅጣት የሚያስከትሉ የፓርቲውን የመተዳደሪያ ደንብ የተለያዩ ድንጋጌዎችን በመጣሳቸው ፣ የፓርቲውን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመገኝታቸው እና አሁንም ከጥፋት ድርጊታቸው ሊታረሙ ባለመቻላቸው ፤ በዚህም መሰረት ስማቸው ከላይ የተዘረዘረው ከድርጅት አባልነታቸው የታገዱ ሲሆን ፣ በቀጣይም የፈጸሟቸው ዝርዝር ጥሰቶችን የተመለከቱ ማስረጃዎችን መሰረት ተደርጎ የዲሲፕሊን ክስ እንዲመሰረትባቸውና ክሱም በአስቸኳይ በንቅናቄው የዲሲፕሊን ኮሚቴ በኩል እንዲታይ ተመርቷል፡፡

ሐ. ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠት

  1. አቶ ሀብታሙ በላይነህ መኮንን ፣
  2. አቶ በቀለ ምንባለ አምሳሉ ፣

የንቅናቄው ቋሚ ኮሚቴዎች አባላትና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው እያለ በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አብረው ውሳኔ ያሳለፉበትን አጀንዳ በእጅ አዙር ለመቀልበስ አባላትን በማሳደም ፤ ለንቅናቄው የስብሰባና ሥነስርዓታዊ ህጎች ፣ እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት ባለመገዛትና የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎችን ረግጦ በመውጣት ተደጋጋሚ ጥሰቶችን በመፈፀማቸው ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ተወስኗል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ወቅታዊው ሁኔታ በሚጠይቀው መልክ ተጠናክሮ ለመገኘት ፣ ከግብታዊነት እና ስሜታዊነት ርቆ ፣ በበቂ ጥናት እና ዝግጅት ላይ ተመስርቶ ዘላቂ ድርጅታዊ ማሻሻያ /ሪፎርም/ ለማድረግ የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ይገልፃል፡፡

ከዚህ አኳያ የፓርቲውን አመራር በአቋራጭ በመቆጣጠር ለህዝባችን በጎ ባልሆነ የኃይል አሰላለፍ ውስጥ ለማስገባት የሚደረግ ማናቸውንም ጥረት ፓርቲያችን የማይታገስ መሆኑን እያስገነዘብን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በመሰል ድርጊት ውስጥ ተሳትፎ የምታደርጉ አንዳንድ የፓርቲው አባላት ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ ፓርቲው አስስቧል።

Exit mobile version