Site icon ETHIO12.COM

የመረጃ ሙያተኞች በመረጃ ሙያ ዐይንና ጆሮ ሁኑ

የመረጃ ሙያተኞች የተቋሙ ዐይን እና ጆሮ ሆነው የተጣለባቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በቁርጠኝነት ሊፈፅሙ እንደሚገባ ሌ/ጀኔራል ብርሃኑ በቀለ ገለፁ።

በአዋሽ 7 ጥምር ጦር አካዳሚ ውስጥ የመረጃ ዋና መምሪያ ከተለያዩ የሰራዊቱ ክፍሎች መልምሎ በመረጃ ሙያ ያሰለጠናቸውን አባላት አስመርቋል፡፡

በምርቃቱ መርሃ-ግብር ላይ በትምህርት ቆይታቸው የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የምስክር ወረቀትና ሽልማት በመስጠት የስራ መመሪያ ንግግር ያደረጉት ሌ/ጀኔራል ብርሃኑ በቀለ ናቸው ፡፡

ጀኔራል መኮንኑ በሰጡት የስራ መመሪያ ንግግር መረጃ ማለት የአንድ ተቋም አይንና ጆሮ ነው። ለተልዕኮ ስኬት የመረጃ ሙያተኞች ታላቅ ኃላፊነት የተጣለባቸው በመሆኑ የተቋሙ ዐይን እና ጆሮ ሆነው ግዳጃቸውን በቅንነትና በታማኝነት ሊፈፅሙ ይገባል ብለዋል።

የሀገራችንን ኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት ጠብቆ ለትውልድ ማሻገር የእኛ መከላከያ ሠራዊት አባለት ኃላፊነት ነው ያሉት ጀኔራል መኮንኑ የመረጃ ሙያተኞች በደህንነት ስራ ሀገርን ስታገለግሉ የተጣለባችሁ ኃላፊነት ድርብ በመሆኑ እድለኛ ያደርጋችኋል እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ሌ/ጀኔራል ብርሃኑ በቀለ አክለውም የወታደር ማንነት የሚለካው በብሔሩ እና በክልሉ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነቱ ነው ያሉ ሲሆን ሠራዊቱ ኢትዮጵያን ሉአላዊነቷን እና ደህንነቷን ለመጠበቅ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ለትውልዱ ያስተላልፋል ብለዋል።

ሃገራችን ስትራቴጂካዊ ጠላቶቿን መከላከልና ሉአላዊነቷን ማስቀጠል ቀዳሚ ተልእኳችን መሆኑን ተገንዝባችሁ ኢትዮጵያን የሚያሻግር የመረጃ ኃይል ለመሆን በቁርጠኝነት እና በፍፁም ታማኝነት መስራት ይጠበቅባችኋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ጀኔራል መኮንኑ ለስልጠናው መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለነበራቸው አካላት እና ግለሰቦችም ምስጋና አቅርበዋል።

የስልጠናው አስተባባሪ ሻ/ቃ ያሬድ ሰለሞን ባቀረቡት የስልጠና ሪፖርት ከዚህ በፊት የመረጃ ሙያውን የወሰዱ አባላት ለአዲስ ሰልጣኞች ልምድ እና ተሞክሮ በማስተላለፍ የመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል፡፡

ተመራቂ የመረጃ ሙያተኞች በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው መከላከያ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ለመወጣት የሚያስችል አቅም አግኝተዋል ብለዋል፡፡

Via – ENDF

Exit mobile version