Site icon ETHIO12.COM

ብ/ጄ ተፈራ ህገ መንግስቱን በኃይል በመናድ ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ

/ጄነራል ተፈራ ማሞ ህገ መንግስቱን በኃይል በመናድ ወንጀል ተጠርጥረው ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀድሞው የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ ማሞ ላይ የ10 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ።

ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ባህርዳር በሚገኘው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርበው ነው ፍርድ ቤቱ የ10 ቀናት ቀነ ቀጠሮ የሰጠው።

ዛሬ ጠዋት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብለው የነበሩት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ዛሬ ከሰዓት መልስ መቅረባቸውን ጠበቃቸው አቶ ሸጋው አለበል ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።

ህገ መንገስቱን በኃይል በመናድ ወንጀል በሚል ፍርድ ቤት መቅረባቸውንም ነው ጠበቃው የተናገሩት።

ፖሊስ ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ለ14 ቀናት ታስረው እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱን የጠየቀ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ 10 ቀን ብቻ በመፍቀድ ለግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱንም አቶ ሸጋው ተናግረዋል።

የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ ማሞ ባሳለፍነው ሰኞ በአዲስ አበባ ባልታወቁ ሰዎች መታፈናቸው ይታወሳል።

ቆይቶ በወጣ መረጃ ብርጋዴር ጄነራል መኮንኑ ባህር ዳር በሚገኝ አንድ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን ጠበቃቸው እና ባለቤታቸው መናገራቸው አይዘነጋም።

ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ ማሞ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ከ 10 ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ “ውጥን አላቸው” በሚል ክስ ተከሰው እስር ላይ መቆየታቸው ይታወሳል።

ለሁለት ጊዜያት የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ በመሆን ያገለገሉት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ሳተላይት ራዲዮና ቴሌቪዥን (ኢሳት) ጋር ቃለ ምልልስ ነበራቸው።

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ለመጨረሻ ጊዜ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ በመሆን የተሾሙት ባለፈው ሃምሌ ነበር፡፡ ከሹመት በኋላም የፌደራል መንግስት ከህወሃት ጋር ባደረገው ጦርነት በፌደራል መንግስት ጦር እዝ ስር በመሆን ውጊያ ሲመሩ፣ ሲዋጉና ሲያዋጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

Source – አል-ዐይን

Exit mobile version