ETHIO12.COM

ሠላም አስከባሪ ወደ ወልቃይት? አውሮፓ ሕብረት ምን እየወጠመደ ነው?

በአማራ ክልል የተነሱ ዓላማቸውና መድረሻቸው ለጤነኛ ዜጎች በግልጽ የማይታይ ግብግቦች ውጤታቸው ” እጄን በጄ” ሊሆን እንደሚችል የሚሰጉ ጥቂት አይደሉም። አመድ ሊያደርገው ከተነሳው ሃይል ተርፎ በማገገም ላይ ያለውን ክልል ዳግም በራሱ ልጆች ለያነዱት ሌት ተቀን የሚተጉ፣ በክልሉ ቋንቋ ” የባንዳ ባንዳዎች” የአቡሻማኔ የጥፋት ግልቢያ ላይ ባሉበት በአሁኑ ወቅት አውሮፓ ህብረት አንዳች ነገር እያሴረ መሆኑ በመረጃ ይፋ ሆኗል። ውሎ አድሮ በገሃድ የሚሰማ እንደሚሆን ይጠበቃል።

አንድ ሆኖ ቀዳዳ በመደፋፈን የአማራ ክልል ሕዝብ በቀዬውና በተበተነበት ሁሉ በሰላም እንዲኖር መስራት ሲገባ፣ እርስ በርስ የሚደረገው የተላላኪነት ፍትጊያ ውጤቱ የከፋ እንደሚሆን በስፋት እየተገለጸ ባለበት በአሁኑ ሰዓት፣ “የህግ የበላይነትን” የተባለው ዘመቻ መጀመሩ የፈጠረው ጫጫታ ምን አልባትም ከዚሁ ከደባው ጀርባ ያለው ሃይል ድንጋጤ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ህብረቱ ተዘጋጅቶ የቀረበለት ሰነድ እስሌማን ዓባይ እንደሚከተለው ሰብሰብ አድሮጎ ያቀረበውን ታነቡ ዘንድ እጋብዛለሁ።

የአውሮፓ ህብረት ምናብ በሰሞንኛ አካሄዱ – የዓባይ ልጅ እስሌማን ዓባይ

የአፍሪካ ቀንድን በተመለከተ አውሮፓ ህብረት ከትላንት በስቲያ አንድ ጥናታዊ ሰነድ ተረክቧል። ጥናቱ ካሲዮ ማሲሞ ካስታልዶ በተባሉ ጣልያናዊ ፕሮፌሰር ተደራጅቶ ነው ለህብረቱ ፕሬዝደንትና ምክትል እንዲሁም ለህብረቱ ኮሚሽን ገቢ የሆነው። ፕሮፌሰሩ በአርመን እና አዘርባጃን አወዛጋቢ መሬቶች ላይ መሰል ሚና እንደነበራቸው ሙያዊ ታሪካቸው ያመላክታል።
የፖሊሲ መነሻ የሆነው ጥናታዊ ሰነዱ አውሮፓ ህብረት በአፍሪካ ቀንድ በቀጣይ ፖሊሲዎቹ ላይ በሚከተላቸው ውሳኔዎቹ ላይ ግብአት ይሆን ዘንድ የተዘጋጀ ነው። አንድ መቶ ሰላሳ ገፅ ያሉት ሰነዱ በደቡብ ሱዳን በሱዳን በሶማሊያ በሶማሊላንድ በጂቡቲ እና ኤርትራ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የዳሰሰ ነው በሚል ቀርቧል። ከሌላው በበለጠ ቁጥር በሰነዱ ኢትዮጵያ የሚለው ስም 71 ጊዜ ተጠቅሷል።

ሰነዱ በተጠቀሱ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የተከሰቱ ያላቸውን የድርቅ ጦርነት ድህነት የመሳሰሉ ችግሮችን ህብረቱ ለመፍታት ምን ማድረግ እንዳለበት የማመላከት ግብ የተቀመጠለት ነው። ይሁንና በቀጣናው የተከሰቱ ያላቸውን የሰብአዊ መብት እና የግጭት አዝማሚያዎች በሚል ያስቀመጠው ድምዳሜ የምእራባዊያን ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝና የሚያበረታታ ሆኖ ይገኛል።
ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣይ የፀጥታ መደፍረስ የህወሃትና የኢትዮጵያ መከላከያ ፍጥጫ (በወልቃይት መሆኑ ነው) የህዳሴ ግድቡ ድርድር እልባት ማጣት እና የአልሸባብ መነቃቃት እንዲሁም የኢትዮ ሱዳን የአልፋሻቃ ውጥረት ከተጠቀሱት መካከል ይገኛሉ። ለህብረቱ የቀረበው የፖሊሲ ምክረ ሀሳብ ታዲያ እንደ ወረደ ባይሆንም የሰላም አስከባሪ ስምሪትን ሀሳብ የሚማፀን ነው።

ለምሳሌ ጂቡቲ በቀጠናው የፀጥታ ችግር እንደሌለባት በመግለፅ ነገር ግን አልሼባብ ከሚያሳየው የስጋት ሁኔታ አንፃር የሰላም ማስከበሩ በአለማቀፍ ተጨማሪ ወታደራዊ ስምሪት መደገፍ አለባት ይላል።
ይኸው ሰነድ ስለ አፍሪካ ቀንድና ቀይ ባህር ቀጣና በህብረቱ የተደረጉ ስትራቴጂክ ጥናቶችን መሰረት በማድረግ ቀጣናው ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊያችን ነው ሲል ያሰምርበታል። ተግዳሮት የሆነባቸው ደግሞ የቻይና በቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ እየሆነች መምጣቷ ነው ይላል።


እነዚህን አመላካቾች ገጣጥመን ስንመለከት የሰላም አስከባሪ በቀጣናው በተለይም በወልቃይት አካባቢ የማስፈር እቅድ መያዙን መገመት ያስችላል። ኢትዮጵያን 71 ጊዜ የጠቀሰው ሰነዱ ቀጣይ ምክክሮቻቸው ደግሞ ለተፈፃሚነቱ ውሳኔ ማሳለፊያ ይሆናሉ ማለት ነው። ይህንኑ ለማጠናከር በአውሮፓ ከሚገኝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከአንደኛው የደረሰኝን የስጋት ማስጠንቀቂያ ጠቅሼ ብቻ ልለፍ።

ይኸውም የአውሮፓ ህብረት ጥናታዊ ሰነድ ጋር ባለስልጣኖቻቸው ሰላም አስከባሪ በወልቃይት ስለ ማስፈር አላማ የሰነቀ አጀንዳ ላይ መሆናቸውንና ተከታታይ መድረኮች አዘጋጅተው እየመከሩበት ናቸው ይለናል። በይፋዊ ሰነዱ ላይ የተቀመጡ የፀጥታ ስጋት አዝማሚያዎቻቸው በርግጥም አመላካቾች ናቸው።

በህዳር 202 ጦርነቱ ሲጀመር ህወሃት የጣሰው አለማቀፍ ህግ አልጠቀሱም። ይልቁንም የኢትዮጵያ ጦር በትግራይ መግባቱን ተከትሎ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሞት ረሃብና በደል መከተሉን ብቻ ገልጿል። ህወሃት በቀጣይ ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር ሌላ ውጊያ ሊከፍት ነው የሚለው ስጋታቸውና ለዚህም በመፍትሄነት ያስቀመጡት መፍትሄ በተቃራኒው ለሌላ ቀውስ የሚዳርግ ነው። ስጋቱን ለማስወገድ ህወሃትን ከፌደራል መንግስቱ ጋር በእኩል ሚዛን ባለድርሻ ከማድረጉ ባለፈ ከአፍሪካዊ አማራጮች ጋር አለማቀፍ ጣልቃ ገብነት በመፍትሄነት ተዘርዝሮ ይገኛል።

ከዚሁ ጋር የአልፋሻቃ መሬትን በተመለከተ የተጋነኑ የስጋት ነጥቦች የተጠቃቀሱ ሲሆን ይህም በወልቃይት ሰላም አስከባሪ ቢገባ ከህወሃት የሚቃጣውን ጦርነት ብሎም ሱዳንን ሊጨምር የሚችለው ቀጣይ ምናባዊ ጦርነት ለማስወገድ መፍትሄ ይሆናል እያሉ ይመስላል። ከላይ እንደተጠቀሰው አውሮፓ ህብረት ለቀይ ባህርና ምስራቅ አፍሪካ ጠቀሜታ ከመቼውም በላይ ትኩረት እሰጣለሁ ብሏል። ስጋታቸው የቻይና በአካባቢው መስፋፋት ነውም ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የህወሃትን ህልውና ለስትራቴጂክ አላማቸው ማሳኪያነት መመኘታቸው የዘንድሮ ሳይሆን ነባር ታሪካቸውም ነው። ወልቃይት ለም እና ውሃ ገብ የሆነ ሀብታም ምድር ከመሆኗ ባለፈ ለህወሃት ድንበር ተሻጋሪ ሴራ እስትንፋስ መሆኗንም መዘንጋት የለብንም። ሰላም አስከባሪ ሀይል በወልቃይት ተሰማራ ማለት ደግሞ ህወሃት አፈር ልሶ ይነሳል። የምእራባዊያኑ ቀጣናዊ ምኞትም ህወሃት ህላዌ ይኖረው ዘንድ ተስፋ ማድረጋቸውም ከተጨባጭ ነጥቦች የተቀዳ መሆኑን ልብ ይሏል።

ህወሃት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ጀምሮ ነው የወልቃይትን ጠቀሜታ የተረዳው ይባላል። በወቅቱ ወደ ሱዳን በመጓዝ ድጋፍና የመንቀሳቀሻ ቀጠና ያገኝ ዘንድ የግድ ነበር። ነገር ግን በወቅቱ የጀብሃ ነፃ መሬት አማራጩ ነበርና ማለፍ የሚችለው ከያዘው ቁሳቁስ ሁሉ ግማሹን ከፍሎ ለጀብሃ ማካፈል ሲችል ብቻ ነበር። ህወሃትም ወልቃይትን ከለምነቷ ባለፈ ስትራቴጂክ ፋይዳዋን በተጨባጭ መገንዘብ ጀመረ ማለት ነው። በህወሃት ትግል ወቅት CIA ራሱ ወልቃይትን አንዷ የቅኝት ቀጣና ስለማድረጉ ድርሳናት ያወሳሉ።

የኢትዮ ሱዳን ውዝግብ መነሻ የሆኑት ያካባቢው መሬቶች የግጭት ቀጠና ሆነው መቀጠላቸው ዐማራውን ብሎም ኢትዮጵያን ከጎረቤት ድንበር ለመነጠል እንደሚጠቀምበትም በርካቶች ይገልፃሉ።
ህወሃት በሱዳን ምድር ተገኝቶ ወታደር ማሰልጠን የቻለው፤ በቤንሻንጉል ጉምዝ በአማራ በጋምቤላና ብሎም ኦሮሚያ ድረስ ቅጥረኛ እየላከ ሽብር ለመፈፀምና ለማስፈፀም ያለ ወልቃይት ኮሪደርነት የማይቻል ነው ይላሉ ጉዳዩን በውል የተገነዘቡ ፀሃፍት።
ይህን ታሪካዊ ተጨባጭ ይዘን አውሮፓ ህብረት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ያሰናዳው ጥናትንም ሆነ ጥናታዊ ምክረ ሀሳቦቹን ተከትለው በሚደረጉ የፖሊሲ ወሳኔዎች ላይ ወልቃይት ላይ ሰላም አስከባሪ የማሰማራት፤ በዚህም ለህወሃት ስትራቴጂክ አድሎ በማድረክ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በመዳፋቸው የማስገባት ህልም ላይ ናቸው ማለት ነው።

አፍሪካዊያን ለአሜሪካ ያላቸው የመረረ ቃውሞ ከሌላው ወቅት የከፋ በሆነበት በዚህ ወቅት በአውሮፓ ህብረት አንፃራዊ የዲፕሎማሲ ምቹ ሁኔታ በኩል የዋሽንግተን ሴራ ከአፍሪካ ቀንድ ጋር አስሮ ሊጠመዝዘን እያደባ መሆኑንም መዘንጋት አይኖርብንም።
መሰል ጣልቃ ገብነቶች የወልቃይት ጉዳይ በውል ባለመገንዘብ አሊያም ሆን ተብሎ በታቀደ መንገድ ኢትዮጵያን ቅኝ የመግዛት ስትራቴጂ መሆኑን በመገንዘብ ከዛሬው እለት ጀምሮ ስራዎች መስራት ከኢትዮጵያውያን ይጠበቃል[በተለይም በአውሮፓ በሰሜን አሜሪካ እና በሌሎችም ሀገራት በሚገኙ አትዮጵያዊያንና ዲያስፖራዎች በኩል።]
ኢትዮጵያዊያን(ኤርትራዊያን ጭምር) የተሸረበባቸውን የድህረ ቅኝ አገዛዝ ሴራ ለመመከት በዲጂታል ዘመቻውም ሆነ በሁሉም አውድ በፅኑ አቋም ህብረት የምናሳይበት ጊዜ መሆኑም ይሰማኛል።

ዋቢዎችን ጨምሮ ለማንበብ ⬇️

https://eslemanabay.com/peace-keepers-welkait-wolkait-%E1%8B%88%E1%88%8D%E1%89%83%E1%8B%AD%E1%89%B5/
Exit mobile version