Site icon ETHIO12.COM

በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች ሁሉ የትህነግ እጅ እንዳለባቸው በመረጃ ተረጋገጠ

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው ከነበሩ ግጭቶች ጀርባ የአሸባሪው ሕወሓት እጅ እንዳለበት በምርመራ መረጋገጡን ፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ። በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የግጭትና አለመረጋጋት ክስተቶች መስተዋላቸው ይታወቃል።

በተለያዩ ምክንያቶች በተከሰቱት ግጭቶች የበርካታ ወገኖች ህይወት ሲያልፍ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀልም ተከስቷል። በእነዚህ ወንጀሎች ላይ ተሳታፊ የነበሩ አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ፍትህ እንዲያገኙ መሰራቱን ፍትህ ሚኒስቴር ገልጿል።

የፍትህ ሚኒስትር ደኤታ ፍቃዱ ጸጋ በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶችን መንስኤ ለማጣራትና ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በተደረገው ምርመራ የአሸባሪው ሕወሓት የጥፋት እጆች መኖራቸው ተረጋግጧል ብለዋል። አሸባሪው ሕወሓት ግጭቶችን በጦር መሳሪያና በበጀት በመደገፍ እንዲሁም ስምሪት በመስጠት ስለመሳተፉ በመረጃና ማስረጃ መረጋግርጡንም አመልክተዋል።

”እኔ ያልመራኋት አገር መቀጠል የለባትም” ብሎ የተነሳው አሸባሪ ቡድን አገር ለማፈራረስ የተለያዩ የጥፋት አማራጮችን መጠቀሙን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የፍትህ ሚኒስቴር ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በቴፒ፣ በቡራዩና በአዲስ አበባ፣ በአሶሳ እና ሌሎችም አካባቢዎች የተፈፀሙ ወንጀሎች ተጣርተውና ምርመራ ተደርጎ ውሳኔ እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልጸዋል።

በጌዲዮና ጉጂ እንዲሁም በሀዋሳ በተፈጠሩ ግጭቶች የወንጀሉ ተሳታፊ የነበሩ አካላትም የፍርድ ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል። መነሻቸውን የሃይማኖትና የወሰን ጉዳይ አድርገው በቅርቡ የተከሰቱ ወንጀሎችን የሚመረምር ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን ጠቁመዋል።

በጎንደር፣ በደባርቅና በወራቤ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ እንዲሁም በጂንካና ደራሼ ወሰንን መነሻ አድርገው የተከሰቱ ግጭቶችን በማጣራት ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ሃይማኖትንና ብሔርን መነሻ አድርገው የተከሰቱ ግጭቶች በፌዴራል መንግሥት ብቻ እንዲታዩ መወሰኑን ለኢዜአ ተናግረዋል። ለፍትህ ተደራሽነት ከመስራት በተጓዳኝ በባህላዊ እሴቶች የእርቅ ተግባራት እንዲከናወኑ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የድንበርና የወሰን ጉዳዮችን በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት ይሰራል ብለዋል። የጥፋት ኃይሎች አገር የማፍረስ እንቅስቃሴ አሁንም የቀጠለ ቢሆንም መንግሥት ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማድረግና የህግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትሩን ጠቅሶ የዘገበው ዋልታ ነው።

Exit mobile version