Site icon ETHIO12.COM

ኢሳያስ – ዘመቻው እስከ መጨረሻ ቀብር ይሆናል ሲሉ ትህነግን አስጠነቀቁ

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ቃል አቀባይና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ግጭት እንደነበር ሳይሸሽጉ “እዚህ ግባ የሚባል ግን አልነበረም” ቢሉም የትህነግ የኤርትራ ሃይል በሚገባ መዋጋታቸውን የተለያዩ ወገኖች ሲያስታውቁ ነበር። ቢቢሲ እንዳናገራቸው የጠቀሳቸው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትም ውጊያ መደረጉን አረጋግጠው እንደነበር ይታወሳል።

በተደጋጋሚ ዶክተር ደብረጽዮንና ሌተናል ጀነራል ጻድቃን “ሻዕቢያን አጥፉልን” በሚል ሃያላን ለሚባሉት አገራትና መሪዎች ሲያስታውቁ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። ሁሉም አልፎ “አዲስ አበባ ይገባል፤ ዙሪያውን ከቧል” የተባለለት ትህነግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በመሩት ጦርነት ተሸንፎ ያልተጎዳ ሃይሉን ወደ መቀለ ካስገባ በሁዋላ ከኤርትራ ጋር በኦፊሳል መዋጋታቸው ሲገለጽ ይህ የመጀመሪያ ነው።

“ጦሬ ምንም ሳይሆንና ሳይነካ ይዤ አውቄ ነው ወደ መቀለ የገባሁት” ያለው ትህነግ፣ ኤርትራን መያዝና ደጋማ ክፍሉን ጠቅልሎ “ታላቅ” ያላትን ኤርትራን እንደሚገነባ ደጋፊዎቹን ቁልፍ ሰዎቹ በይፋ ሲናገሩ ቢሰማም እንደ ሰሞኑ ጉዳዩ አልከረረም።

የኤርትራ የደህንነት ክፍል ሙሉ መረጃና የሃይል አሰላለፉን ተረድቶ የተሞከረውን ጥቃት እንዳከሸፈ ቀደም ብለን መጻፋችን ይታወሳል። ኤርትራ ፕሬስ ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ጠቅሶ ይፋ እንዳደረገው

“አሸባሪው ሕወሓት ኤርትራን ምድር ከረገጠ የቡድኑን ኣባላት ጠራርገን አርቀን የምንቀብርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም!” ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጠቅሶ” በመንደፈራ፣ ፆሮና እና ባድመ ከተሞች ኣቅጣጫ ከኤርትራ የድንበር ጠባቂዎች ጋር ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን ሞክሮ እየተመታ ተመልሷል። በተለይም በመንደፈራ ኣቅጣጫ በወታደሮቻችን ላይ ዓለማቀፍ የምርኮኛ ሕግን በመጣስ የጦር ወንጀል ፈጽሟል” ማለታቸውን አስነብቧል። “ዓለማቀፍ የምርኮኛ ሕግን በመጣስ የጦር ወንጀል ፈጽሟል” ሲሉ መቼና እንዴት የኤርትራ ሰራዊት አባላትን እንደማረካቸው፣ በምን ሁኔታ እንደማረካቸውና ምን አይነት የመብት ጥሰት እንደፈጸመ ኤርትራ ፕሬስ አላብራራም።

«አሸባሪው ሕወሓት የጋላቢዎቹን ተልእኮ ተቀብሎ ለማስፈፀም እና የኤርትራን ሕዝብ አንገት በማስደፋት የባሕር በር ለመያዝ ከፍተኛ ወታደራዊ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ እናውቃለን” ሲሉ የድህንነታቸውን መረጃ ዋቢ ያደረጉት ኢሳያስ፣ “በመንደፈራ፣ ፆሮና እና ባድመ ከተሞች ኣቅጣጫ ከኤርትራ የድንበር ጠባቂዎች ጋር ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን ሞክሮ እየተመታ ተመልሷል። በተለይም በመንደፈራ ኣቅጣጫ በወታደሮቻችን ላይ አለማቀፍ የምርኮኛ ሕግን በመጣስ የጦር ወንጀል ፈጽሟል” እንዳሉ ዘገባው አስታውቋል።

“እኛ የወንበዴው ቡድን የሆነውን የሕወሓትን ሰይጣናዊ ድርጊት ይዘን የምንከስበት እና የምንወቅስበት ኣካሔድ ኣይኖረንም። የሽብር ቡድኑ ዝግጅቱን ኣጠናቅቆ ወደ ኤርትራ ምድር ከረገጠ ግን የቡዱኑን ኣባላት ጠራርገን አርቀን የምንቀብርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም” በማለት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ዝተዋል። ጦርነቱ ከተጀመረ እስከ ቀብር እንደሚሆን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ከትህነግ በኩል ቃል በቃል መልስ አልተሰጠም። ዘወትር ግን “የአምባ ገነን ፉከራ” የሚል ተመሳሳይ ምላሽ ለፕሬዚዳንቱ እንደሚያቀርቡ ይታወቃል።

“ኤርትራ ሉኣላዊነቷን ለመዳፈር ለሚሞክሩ ተላላኪዎች ከበቂ በላይ ምላሽ መስጠት የሚችል ኣስተማማኝ የጦር ሓይል እና ሕዝብ ኣላት።» ሲሉ ግንቦት 24/2022 አቶ ኢሳያስ ለሰነኣ ጋዜጣ የሰጡትን ቃል መጠይቅ ዋቢ አድርጎ ኤርትራ ፕሬስ አስነብቧል።


Exit mobile version