ETHIO12.COM

የመሰረተ ልማት ቀበኞች ላይ ” የሞት ቅጣት”

አስናቀ አያሌው የተባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ ” በመሰረተ ልማት ዝርፊያና ማውደም ላይ የተሰማሩ ዜጎች ለአገር አይጠቅሙም” ባይ ናቸው። ስርቆት በትምህርትና በተመጣጣኝ ቅጣት ማረቅ እንደሚቻል እንደሚያምኑ ገልጸው፣ የኤለኤክትሪክ ምሶሶ በማውደም ከተማ የሚያጨለሙ፣ የሆስፒታልና የመሰረታዊ አገልግሎት በሚያቋርጡ፣ የባቡር መስመር በተደጋጋሚ የሚቆርጡ ግን ከተራ ሌብነት በተለየ ሊታዩ እንደሚገባ ይገልጻሉ።

“አንድ ወረዳ ወይም ከተማ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ስንት ወላድ አገልግሎት አጣች ወይም ሞተች?” ብሎ ማስላት አግባብ እንደሚሆን፣ በተደጋጋሚ የባቡር መሰረተ ልማት ዝርፊያ በመካሄዱ ስንት ባለሙያዎች በምድብ ስራቸው መገኘት አልቻሉም? ምን ያህል ተገለጋዮች አገልግሎት አጥተዋል? ጉዳቱ ከገንዘብ ኪሳራ በላይ ከህይወት ጋር ተዳምሮ ቢጠና አስደንጋጭ ውጤት እንደሚገኝ አቶ አያሌው በላኩልን ማስታወሻ ጠቅሰዋል።

“አንድ ሰው” አሉ ሙያቸውን ሳይገልጹ ማስታወሻቸውን የላኩት አቶ አይሌው፣ “አንድ ሰው ከፍተኛ ሃይል ተሸካሚ የኤለኢክትሪክ መስመር ለመቁረጥና ለመዝረፍ ሲወስን ለህይወት ያለው ግምት የተበላሸ፣ ምን አልባትም ህይወትን ምን እንደሆነ ያልተረዳ ነው። በቡድንም ሆነ በድርጅት ደረጃ በዚህ መልኩ የሚያስቡ ከህይወት ፍሬ የጎደሉ ናቸውና ህጉ እንዲህ ያሉትን የማጥራትን እርምጃና ለሌሎችም በአስደንጋጭ መልኩ ትምህርት ሊሰጥ በሚችል መልኩ መሆን አለበት” ሲሉ ግልጽ የስነልቦናና የፍትህ አካላት ውይይት ሊያደርጉበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ የባቡር አገልግሎት ትናንት፣ ሰሞኑንን ደግም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ሙሉ በሙሉ አንድ አውራጃ ኤሌክትሪክ መቋረጡን ገልጾ ይፋ ያደረገውን ዘገባ ከተመከቱ በሁዋላ አሳባቸውን ለማጋራት በሁለት አንቀጽ አስረው በላኩት ማስታወሻ፣ ” ይህ መክሸፍ ነው። ይህ የትውልድ ውድቀት ነው። ሰዎች በአስገዳጅ ሁኔታ ሊሰርቁ ይቻላሉ። መሰረት ልማት ማውደም ግን ምህረት አልባ ወንጀል በመሆኑ እርምጃው የከረረ መሆን አለበት። ሕዝብም ተባባሪ መሆን አለበት። እንዲህ ያሉ የሞራል ምች የመታቸውን ጥቂት ማጅራት መቺዎች አስሮ መቀለብ እንደ አገር ማጅራት መቺዎችን ማስፋፋት እንጂ ሌላ ውጤት አያስገኝም” ብለዋል። ዛሬ ኦቢኤን ያተመውንና አቶ አያሌው አያይዘው የላኩትን ዜና ከስር ያንብቡ።

በባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የፊንፊኔ ቀላል ባቡር አገልግሎት ገለጸ፡፡

የፊንፊኔ ቀላል ባቡር ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቡልቱማ ቂጣታ÷ለባቡር በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል የሃገርን ኢኮኖሚ ወደኋላ ከማስቀረቱም በተጨማሪ በከተማዋ ያለውን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እያስተጓጎለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ 16 ሺህ 402 ሜትር የሚረዝም የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብል ስርቆት መፈጸሙን ጠቁመው፥ በዚህም 26 ሚሊየን 94 ሺህ 75 ብር የሚገመት ኪሳራ በተቋሙ ላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡

አብዛኛው የባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆት እየተፈፀመ የሚገኘው በቂርቆስ፣ በንፋስ ስልክ፣ በየካ፣ በልደታ፣ በአቃቂ ቃሊቲ እና በለሚኩራ ክፍለ ከተሞች መሆኑን የገለፁት አቶ ቡልቱማ÷ በዚህ ሳምንት ብቻ መሪ ሎቄ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ፣ ልደታ እና ሳሪስ አቦ አካባቢ ከመሬት በታች በተዘረጉ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብሎች ላይ ስርቆት እና ውድመት መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ እየተባባሰ የመጣውን የባቡር የኤሌክትሪክ ኬብል ስርቆት ለመከላከል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ቢሆንም ድርጊቱን በሚፈፅሙ ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪ ባለመሆኑ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንም ነው የተናገሩት።

እኩይ ተግባሩን ለመከላከል የፊንፊኔ ከተማ አስተዳደር ለጉዳዩ የተለየ ትኩረት በመስጠት ተገቢ የሆነ ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርግና ድርጊቱን በሚፈፅሙ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል፡፡

የፊንፊኔ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕግ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታሪኩ ማዕረጉ በበኩላቸው÷ በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀምን የስርቆት ድርጊት ለመከላከል የተለያዩ አዋጆች በስራ ላይ ቢውሉም በፊንፊኔ ቀላል ባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደመጣና ከፍተኛ የሃገር ሃብት እየተዘረፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆት ሲፈፅም የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በሃገሪቱ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 669 መሰረት በከባድ ስርቆት ወንጀል ተከሶ ከ15 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል ብለዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት 11 ወራት በተደረገ ክትትልና የማጣራት ስራ በፊንፊኔ ከተማ ቀላል ባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ በቁጥር ከ37 በላይ ‘’የስርቆትና ጉዳት ማድረስ’’ የወንጀል ተግባራት ተፈፅመው ለተለያዩ የክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች ክስ ተመስርቶ በምርመራና በፍርድ ሂደት ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።

በመሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀም የስርቆት ተግባር ለሃገር፣ ለተቋምና ለማህበረሰብ ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን እንደራሱ ንብረት አድርጎ ሊጠብቅና ይህን መሰል እኩይ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦችን ሲመለከት በተቋሙ 905 ነጻ የጥሪ ማዕከል ጥቆማ ሊሰጥ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ሊያሳውቅ ይገባል ማለታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል።


Exit mobile version