ETHIO12.COM

ፖሊስ በዕቅድ በአዲስ አበባ ሊፈጸም የነበረ የሽብር ተግባር ማክሸፉን አስታወቀ፤ ከ380 በላይ ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል

አልሸባብ በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ ሊፈጽም የነበረው የሽብር ተግባር መክሸፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ የፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ ባካሄዱት ዘመቻ ነው የሽብር ቡድኑን ተግባር ማክሸፍ የተቻለው። ከዚህም በተጨማሪ ሃይማኖትን ተገን አድርገው በነጻ ፕሬስ ስም፣ ከትህነግ ተልዕኮ ወስደው አዲስ አበባ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ340 በላይ ተጨርጣሪዎች መያዝቸው ተመልክቷል።

የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ የሥራ ኃላፊዎች በጋራ በሰጡት መግለጫም ሸኔን ጨምሮ የህወሓት ተላላኪዎች በመዲናዋ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ፣ በሌብነት/ሙስናና በሕገ ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ከ340 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የህዝብን ሰላም እና ደህንነት ለማደፍረስ በአዲስ አበባ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ340 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቁ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ነጋሽ እንደገለፁት የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት በሚያዚያ ወር አጋማሽ የህግ ማስከበር ስራ እንዲሰራና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታውሰው ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት አዲስ አበባ ላይ ትኩረት ሰጥተው ጠንከር ያለ የህግ ማስከበር ስራ ሰርተዋል።

በጦር መሳሪያ ጭምር ተደራጅተው ዝርፊያ የፈፀሙ፣ ተሽከርካሪዎችን የዘረፉ እንዲሁም በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጪ በመደበቅ በዝርፊያ ላይ በተሰማሩ ቡድኖችና ግለሰቦች ላይ ጠንካራ የክትትልና የምርመራ ስራ ተሰርቶ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

እንደ ምክትል ኮሚሽነር ሐሰን ገለፃ ከግለሰብና ባንክ ዘረፋ ጋር በተያያዘ 10 ተጠርጣሪዎች፣ ከመኪና ስርቆት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ 22 ተሽከርካሪዎችን የዘረፉ 33 ተጠርጣሪዎች ከነግብረአበሮቻቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

የሚዲያን ነፃነትን ተገን በማድረግ ህዝብን ከህዝብ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨትና ሀገርን ለማፍረስ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ሽብር ሲነዙ የነበሩ በርካታ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውለን ለህግ በማቅረብ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የታክቲክ ወንጀል ምርመራ ምክትል ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አበበ በበኩላቸው የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማወክ ከተንቀሳቀሱና ከአልሸባብ የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸው 84 ግለሰቦችን ከሶማሌ ክልል ፖሊስ ጋር የጋራ ስራ በመስራት በቁጥጥር ስር አውለናል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከሸኔ የሽብር ቡድን ተልዕኮ ተቀብለው በህቡዕ ሲንቀሳቀስ የነበሩ ግለሰቦች ተይዘው በምርመራ እያጣራን እንገኛለን ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ለማወክ የተንቀሳቀሱ የሀይማኖት አክራሪዎችን በቁጥጥር ስር አውለን በምርመራ እያጣራን እንገኛለን በማለት ተናግረዋል።

መንግስት ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው የወንጀል ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሙስና መሆኑን አንስተው እነዚህን ወንጀሎች የሚፈጽሙት አብዛኞቹ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉና የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው የግል ጥቅማቸውን ለማርካት ሲሉ ከሌሎች ህገ-ወጥ ግለሰቦች ጋር በጥቅም በመመሳጠርና ከደላሎች ጋር በመገናኘት በሀገሪቱ መልካም አስተዳደር እንደሌለ ለማስመሰል ህዝቡ አገልግሎት ሲፈልግ ከመንግስት ጋር ለማጋጨት መብቱን በገንዘብ እንዲገዛ እያደረጉ የሙስና ወንጀል እየተፈፀሙ ይገኛል ሲሉ ገልፀዋል።

ከኢኮኖሚ አሻጥር ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የህዝብ እና የመንግስት ሀብትን ለመመዝበር ከባለስልጣናት ጋር ተመሳጥረው በሙስና ወንጀል ከ580 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ የመንግስት ባለስልጠናት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልፀዋል።

በባንክ ዘረፋ ላይ የተሰማሩና በሞባይል ባንኪንግ አንዳንድ የስነ ምግባር ችግር ያለባቸውን ከውስጥ የባንክ ባለሙያዎች በመያዝ የባንኩንም ጥቅም አሳልፈው በመስጠት ወንጀል ላይ የተሰተፉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውለን በህግ ተጠያቂ አያደረግን እንገኛለን ብለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በመሬት ወረራ ላይ ሰፊ ወንጀል እየተፈመ እንደሆነ ተናግረው በዚህ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦችንም ባደረግነው ክትትል ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ በአብያተ ክርስቲያናት ህንፃ ላይ በመከራየት ፀበልተኛ በመምሰል እና ሐሰተኛ መታወቂያ በመያዝ ተደብቀው ወንጀል ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተጠርጣሪዎችንም በቁጥጥር ስር አውለናል ሱሉ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ከአሸባሪው የህወሓት ጁንታ ቡድን ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ሰፊ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን አሁንም እኩይ ዓላማ ያነገቡ ያላቸው የዚህ ፀረ-ሰላም ኃይል ተላላኪ የሆኑ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ግለሰቦች እንዳሉና ከህዝቡ በሚደርሰን ጥቆማ መሰረት ክትትል አድርገን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሳይሆኑ ከአንዳንድ የስነ-ምግባር ችግር ካላባቸው ወረዳ ላይ ከሚሰሩ ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር መታወቂያን በገንዝብ በመግዛት በድብቅ ወንጀል ለመፈፀም ዝግጅት ላይ ያሉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውለን ምርመራ እያጣራን እንገኛለን ብለዋል።

ኮሚሽነሮቹ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ በተደረገው የህግ ማስከበር ስራ 340 በላይ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም ህብረተሰቡ በሚያከራያቸው ቤቶች የተከራዩን ማንነት እና እንቅስቃሴ በመቆጣጠር የተለየ ነገሮችን ሲመለከት ለፀጥታ አካላት ማሳወቅ እንዳለበት ማሳሰባቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ዜናው ከፋናና ከአዲስ ዘመን የተጠናከረ ነው።


Exit mobile version