ETHIO12.COM

“እኛ ምንም የምናውቀው ነገር የለም፤ የሚያጣሉን ፖለቲከኞች ናቸው” የወዳጃቸውን የአደራ ቤት የመለሱ የቅማንት ተወላጅ

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ጭልጋ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሀብታሙ ፈለቀ የ55 ዓመት ጎልማሳ ሲሆኑ በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚነሱት ግጭቶች ተረጋግተው እንዳይኖሩ ሲያደርጓቸው እንደቆዩ ይገልጻሉ።

በሌሎች ጊዜያት ከተነሱት ግጭቶች በላይ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ 2013 ዓ.ም የተነሳው ግጭት አቶ ሀብታሙን ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል። ሚያዚያ 2013 ዓ.ም ግጭት ተነስቶ ንብረት ሲወድምና የሰው ህይወት ሲጠፋ አቶ ሀብታሙ አካባቢውን ለቀው ለመሄድ መነሳታቸውን ይናገራሉ።

አቶ ሀብታሙ የአማራ ብሔር ተወላጅ ሲሆኑ ቤት ንብረታቸውን ለቅማንት ብሔረሰብ ተወላጁ ጓደኛቸው አስረክበው ወደ ጎንደር ከተማ እንደመጡ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።

ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረው ግጭት በማንነት ምክንያት ሆኖ ሳለ የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑት አቶ ሀብታሙ ቤት ንብረታቸውን እንዲጠብቁላቸው አደራ የሰጡት ግን ለቅማንት ማህበረሰብ ተወላጁ ሀብቱ በላይ እንደሆነ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።

አል ዐይን አማርኛ፤ የጓደኛቸውን ቤት ላለፉት ወራት በአደራ መልክ ጠብቀው ያቆዩትና ትናንት ያስረከቡት አቶ ሀብቱ በላይ በስልክ አነጋግሯቸዋል። ላለፉት ወራት የጓደኛቸውን ቤት እንደራሳቸው አድርገው ከዘረፋና ከውድመት ሲጠብቁ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ግለሰቦች በዚህ ልክ አደራ የሚሰጣጡ ከሆነና የሚደማመጡ ከሆነ እንዴት በሁለቱ ወገኖች መካከል ግጭት ተከሰተ ሲል አል ዐይን ላቀረበው ጥያቄ አቶ ሀብቱ “እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤ የሚያጣሉን ፖለቲከኞች ናቸው፤ ቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቅዴፓ) የሚባል ቡድን የችግሩ ጠንሳሽ ነው” ሲሉ ነው የቅማንት ብሔረሰብ ተወላጁ የገለጹት።

ከስምንት ዓመት በፊት በማንነት ምክንያት እንደተነሱ በተገለጹ ግጭቶች አቶ ሀብታሙን ጨምሮ በርካቶች መፈናቀላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ከ 11 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል ተብሏል።

ነዋሪዎቹ ወደ አይከል ሲመለሱ የከተማው ነዋሪዎች አቀባበል እንዳደረጉላቸው አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል። አቶ ሀብታሙ ከተፈናቀሉበት አካባቢ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ከመመለሳቸውም በላይ በአደራ መልክ የሰጡት ቤታቸውን እንደነበረ መቀበላቸውን ገልጸዋል።

በግለሰብና በህዝብ መካከል ምንም ችግር እንደሌለ የእርሳቸውና የአቶ ሀብቱ ንግግርና አደራ ማክበር ብቻውን ማሳያ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ከአይከል ከተማ ተፈናቅለው የነበሩት ሌላኛው ግለሰብ አቶ ሽኩር መሐመድም ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል። ወደ ከተማ ሲመለሱም ቤትና ንብረታቸውን በሰላም እንዳገኙት ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።

አማራ እና ቅማንት በሚል ሕዝቡ እንዲጋጭ የተደረገው “የቅማንት ኮሚቴ” ተብሎ በሚጠራው ቡድን እንጅ በሕዝብ መካከል እንዳልሆነም ነው አቶ ሽኩር ያነሱት።

ወደ ቀያቸው የተመለሱት ተፈናቃዮች ጊዜያዊ ድጋፍ እና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መንግሥት ሊሰራ እንደሚገባ አንስተዋል።

የአይከል ከተማ ሰላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ሃላፊ መላኩ አለም አንተ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአካባቢው ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በተከሰቱ ግጭቶች ከአካባቢ ርቀው የነበሩ ዜጎች ዛሬ አይከል ከተማ መግባታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጠዋል።

አቶ መላኩ እንዳሉት ግጭቶቹ በተቀሰቀሱ ጊዜ አካባቢውን ለቀው ከተፈናቀሉ ዜጎች በተጨማሪም እጃቸው እንዳለበት የሚጠረጠሩም ወደ ከተማዋ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በግጭቶቹ እጃቸው እንዳበት የሚጠረጠሩ ዜጎች “መንግሥት በሚጠይቀን ለመጠየቅ ዝግጁ ነን” በማለት እጃቸውን ለመንግሥት እንደሰጡም ሃላፊው ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።

ዜጎቹ ወደ አይከል ከተማ የተመለሱት አካባቢው ከግጭት ነጻ መሆኑ ለተፈናቃዮች በመገለጹ ሲሆን የከተማዋ ነዋሪዎችም የተፈናቀሉት ወገኖች እንዲመለሱ በመጠየቃቸው መሆኑ ተገልጿል።

በአማራ ብሔር እና በቅማንት ብሔረሰብ መካከል ግጭት እንዲነሳ ያደረገው ትህነግ መሆኑን አቶ መላኩ ገልጸዋል። አል ዐይን አማርኛ ግጭት ቀስቃሹ ትህነግ ስለመሆኑ ምን ማስረጃ እንዳላቸው የጠየቃቸው አቶ መላኩ፤ ለዚህ ማሳያ መኖሩን ገልጸው ዝርዝሩ ግን ለህግ የሚቀርብ እንደሆነ ገልጸዋል።

 “የቅማንት ኮሚቴ” በሚል ይጠራ የነበረው ቡድን ከትህነግ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደነበረው ያነሱት ሃላፊው፣ የኮሚቴ አባላት ነን ያሉ አካላት ለህክምና በሚል ወደ ትግራይ መሄዳቸው መረጋገጡን አንስተዋል።

የኮሚቴው አባላት ህክምና መሄድ አስፈልጓቸው ከነበረ ቅርብ ወዳሉ የአማራ ክልል የጤና ተቋማት መሄድ ይችሉ እንደነበር የገለጹት አቶ መላኩ ወደ ትግራይ መሄዳቸው ከህወሃት ጋር ግንኑኘት እንዳላቸው ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የአይከል ከተማ ሰላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ሃላፊ መላኩ አለም አንተ “የቅማንት ኮሚቴ” የሚባለው ቡድን ዓላማው ግጭት መፍጠር ነበር ያሉ ሲሆን፤ አሁን ግን በራሱ ጊዜ መፍረሱን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት የቅማንት ብሔረሰብ ተወካይ እንደሆኑ ገልጸው የነበሩ አካላት ቀበሌዎችን እንዲያስተዳድሩ ጥያቄ አቅርበው የክልሉ መንግሥት 42 ቀበሌዎችን እንዲያስተዳድሩ የፈቀደ ቢሆንም ተቃውሞ በመነሳቱ ምክንያት መጨረሻ ላይ 69 ቀበሌዎችን እንዲያስተዳድሩ ተፈቅዶ ነበር። ይሁንና ግጭቱ በዚህም ባለመቋጨቱ ላለፉት 8 ዓመታት ግጭት ሲከሰት ቆይቷል።

የክልል፣ ዞንና ከተማ አስተዳደር የሥራ ሃላፊዎች ከዚህ በኋላ ግጭቱ ዳግም እንዳይነሳ እየተሰራ መሆኑን ደጋግመው ገልጸው የነበረ ቢሆንም ችግሩ ግን ሳይፈታ ቆይቷል። የአይከል ከተማ አስተዳደር ዛሬ እንዳለው ከሆነ ከዚህ በኋላ በአካባቢው ግጭት እንዳከሰት ሕዝቡና የጸጥታ አካላት ከጠዋት እስከ ማታ፣ ከማታ እስከ ጠዋት ስምሪት አድርገው ይጠብቃሉ ብሏል።

የአማራ ክልል መንግሥት በጭልጋና አካባቢው ከሚነሱት ግጭቶች ጀርባ ህወሃት እንዳለበት በተደጋጋሚ ቢገልጽም፤ ህወሃት ግን በአማራ ክልል በሚነሱ ግጭቶች ላይ ግን ምንም ተሳትፎ እንደሌለው ይገልጻል። (አል ዐይን)

Exit mobile version