Site icon ETHIO12.COM

“ በጥቁር ገበያና በባንክ መካከል የተስተዋለው የዶላር ዋጋ ሰፊ ልዩነት ሥርዓት ካልተበጀለት መዘዙ አደገኛ ነው”

የዶላር ዋጋ በጥቁር ገበያና በባንክ ያሳየው ሰፊ ልዩነት ሥርዓት ካልተበጀለት ኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰው መዘዝ አደገኛ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄተስፋ አመለከቱ።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄተስፋ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፣ አሁን በሀገሪቱ ባንኮችን በጥቁር ገበያ የተስተዋለው ከፍተኛ ዋጋ ልዩነት ተገቢው ሥርዓት ካልተበጀለት የሀገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።

ለዶላር ጥቁር ገበያ መፋፋም የተለያዩ ምክንያቶች መጥቀስ ቢቻልም በዋናነት ግን ዶላር በባንክ በኩል በበቂ ሁኔታ ካለማግኘትና እንደ አገር የዶላር አቅርቦት እጥረት የተነሳ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በአሁኑ ጊዜ አንዱ የአሜሪካን ዶላር የባንክ ምንዛሪ ዋጋ 51 ነጥብ 55 ብር ሲሆን በጥቁር ገበያ ግን 78 ብርና ከዚያ በላይ እንደሚመነዘር ገልጸው፤ ይህ ልዩነት መፈጠሩ በሀገራዊ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ከባድ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ተናግረዋል።

ልዩነቱ በዚህ ከቀጠለ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የባሰ አደጋ መደቀኑ አይቀሬ በመሆኑ ጠበቅ ያለ የሕግ ሥርዓት ሊበጅለት ይገባል ብለዋል።

የዶላር ከፍተኛ ዋጋ ጭማሪ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት መንግስት ፍራንኮ ቫሉታ በመፍቀዱ ጋር ምንም ዝምድና የለውም ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፤ ከፍራንኮ ቫሉታ መፈቀድ በፊት የአንድ ዶላር 60 ብር መሆኑ እንዳለ ሆኖ በፍራንኮ ቫሉታ የሚሳተፉ ነጋዴዎች የገንዘብ ምንጫቸው ላይ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ለችግሩ መፍትሔም የሌሎች ሀገራትን አሠራር ማየት ይገባል። ለአብነት ደቡብ ሱዳኖች የዛሬ 20 ዓመት ገደማ በአገራቸው የተስተዋለውን የዶላር እጥረት ችግር በመቅረፍ አቅርቦትና ፍላጎትን ለማቀራረብ የተለያዩ የምንዛሪ ሥርዓት አማራጮችን ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል።

የሱዳን ብሔራዊ ባንክ ዶላርን በገበያው ዋጋ ከደንበኞች ለመቀበል በወሰነው ውሳኔ መሠረት ከውጭ ከሚኖሩ የአገሪቱ ዜጎች በአንድ ጊዜ ቢሊዮን ዶላሮች መሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል። 

አንዳንድ የላቲን አሜሪካ አገሮች እንዳደረጉ ሁሉ ከመደበኛው የዶላር ምንዛሪ ተመን በተጨማሪ ተጓዳኝ የምንዛሪ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ እነዚህና ሌሎች አማራጭ ሥርዓቶች ካልተዘረጉ ችግሩ እየተባባሰ እንደሚሄድ ተናግረዋል።

በጥቁር ገበያ የዶላር ዋጋ ከሚጠበቀው በላይ መናሩና የሀገራቱ ገንዘብ የመግዛት አቅሙ እያሽቆለቆለ በመሄዱ ምክንያት ዚምባብዌና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ለበርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መዳረጋቸውን ገልጸው፤ ችግሩ መላ ሳይበጅለት በዚሁ ከቀጠለም ልክ እንደ ዚምባብዌ ለአንድ የአሜሪካን ዶላር ክምር ብር ማቅረብ የምንገደድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። 

በኢትዮጵያ ፈጣን የማስተካከያ እርምጃ ካልተወሰደ ከጸጥታ አለመረጋጋቱ ጋር ተዳምሮ መዘዙ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ማብራሪያ፣ የዶላር አቅርቦት አማራጮች ላይ ከመሥራት በተጨማሪ ጥቁር ገበያውን ለማክሰም ተዋናዮቹን በማሰር ብቻ ችግሩን መፍታት አይቻልም። ይልቁንም ጠበቅ ያለ የኢኮኖሚና የሕግ ሥርዓት ሊበጅለት ይገባል።

ዋቅሹም ፍቃዱ አዲስ ዘመን

Exit mobile version