Site icon ETHIO12.COM

ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል ከ1 ነጥብ 87 ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ትግራይ ተልኳል

ለትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል ከ1 ነጥብ 87 ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ትግራይ የተላከ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት ለትግራይ ሕዝብ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ መንግሥት ትኩረት በመስጠት ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሮ ድጋፉ እንዲደርስ በማድረግ ላይ ይገኛል።

በክልሉ ለሚገኙ አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ለሚደርሱ ሕዝቦች የገንዘብ፣ የመድኃኒት፣ የተመጣጠነ ምግብ እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች በማድረግ ዜጎች ለከፋ ጉዳት እንዳይዳረጉ በማድረግ ረገድ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሰብዓዊ ድጋፉ በርካታ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ያካተተ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ደበበ፣ 93 ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ተቋማት ምግብና መድኃኒትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ድጋፎችን ለክልሉ ዜጎች በመስጠት ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።

በዚህም እስከ ግንቦት የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ድረስ 1 ነጥብ 87 ቢሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ዝውውር በበርካታ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ ላይ በተሰለፉ አጋር አካላት ለሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት በአየር ትራንስፖርት ወደ አካባቢው ማመላለሳቸውን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ደበበ ገለፃ 202 ሺህ 79 ኪሎግራም የመድኃኒት አቅርቦት በነዚህ የተለያዩ አጋር አካላት ቀርቧል። የተመጣጠነ ምግብ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ደግሞ ከ409 ሺህ 322 በላይ በኪሎግራም ሰብዓዊ አገልግሎት ለሚፈልጉ ወገኖች መደረጉን አንስተዋል።

ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በተመለከተም በነዚህ ሰብዓዊ ድጋፍ በሚያቀርቡት ድጋፍ በኩል 11ሺህ 43 ሜትሪክ ቶን ወደ ትግራይ መላኩን አቶ ደበበ አንስተዋል።

402 ሺህ 229 ሊትር ነዳጅ ወደ መቀሌ ተጓጉዟል። በዚህ አገልግሎት አንድ ሺህ 947 ተሽከርካሪዎች የሰብዓዊ ድጋፉን ያጓጓዙ ሲሆን እስካሁን ድረስ ለሰብዓዊ አገልግሎት የተከናወነ በረራ ደግሞ 223 እንደሆነ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል በሳዑዲ አረቢያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ 102 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለማስገባት በተሠራው ሥራ ካለፈው መጋቢት 21 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ 75 በረራዎችን በማከናወን ከ28 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ተደርጎዋል። በዚህም 25 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች የተመለሱ ሲሆን ቀሪዎቹን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ተግባር የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በኩል የአቀባበል፣ አሸኛኘት፣ የመኝታ፣ የምግብ አቅርቦት፣ የጤናና የስነ-ልቦና፣ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሁም ትምህርት የሚሰጥበትን ሁኔታ ከባለድርሻ መሥሪያ ቤቶች ጋር በመሆን እየተሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በዚህም ከ26ሺህ ስምንት መቶ በላይ ዜጎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተገናኙ ሲሆን ሌሎች መዳረሻቸው ትግራይ ክልል የሆኑ አንድ ሺህ 854 የሚደርሱ ዜጎች በአዲስ አበባ መጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ሙሉውን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ
https://www.press.et/?p=73953

Exit mobile version