Site icon ETHIO12.COM

ከ370 ቢሊዮን ብር በላይ በባንኮች ላይ የማጭበርበር ወንጀል ሙከራ ተደርጓ ከሽፏል፣1.8 ቢልዮን ተዘርፏል

በጥናቱ መሰረት 50 በመቶ ማጭበርበር የተከናወነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን በአቢሲኒያ፣ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል እና ወጋገን ባንኮች ከ1 እስከ 4 ያለውን ደረጃ በመያዝ የማጭበርበር ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ በባንኮች ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ምዝበራ መፈጸሙን ፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ። የፍትህ ሚኒስቴር በባንኮች ላይ የሚፈጸም የማጭበርበር ወንጀል መንስኤና የአፈፃጸም ዘዴን በመለየት የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ የሰራውን ጥናት አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

በውይይቱም የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ ሌሎች የባንክና የጸጥታ ሃላፊዎች ተገኝተዋል። ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ከ370 ቢሊዮን ብር በላይ በባንኮች ላይ የማጭበርበር ወንጀል ሙከራ ተደርጓል።

በዚሁ ሙከራ በተለያዩ ባንኮች ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ማጭበርበር የተፈፀመ ሲሆን ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን በላይ የመዛግብት ምዝበራ መደረጉ በጥናቱ ተረጋግጧል።

በጥናቱ መሰረት 50 በመቶ ማጭበርበር የተከናወነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን በአቢሲኒያ፣ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል እና ወጋገን ባንኮች ከ1 እስከ 4 ያለውን ደረጃ በመያዝ የማጭበርበር ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል።

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ፈቃዱ ጸጋ እንደተናገሩት በባንኮች ላይ የሚፈጸሙ የማጭበርበር ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። የማጭበርበር ወንጀሎች መፈጸማቸው እየተረጋገጠ ቢሆንም የህዝብ ገንዘብ በሚፈለገው ልክ ማስመለስ እንዳልተቻለም ገልጸዋል።

የጥናቱ ዓላማ በባንኮች እየጨመረ የመጣውን የማጭበርበር ወንጀል ውስብስብነት ለማመላከትና በጋራ ወንጀሉን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መፍትሄዎችን ለመሻት መሆኑን ተናግረዋል። የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ በባንኮች ላይ የሚፈጸሙ የማጭበርበር ወንጀሎችን በመለየት የመፍትሄ እርምጃ ሲወሰድ መቆየቱን ገልጸዋል።

ሆኖም የማጭበርበር ወንጀል ሙከራዎቹ እየጨመሩ መምጣታቸውን ጠቅሰው የድርጊቱን አሳሳቢነት በመረዳት መፍትሄ ለማምጣት ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል። ንደ ኢዜአ ዘገባ የጥናት ግኝቶቹን መሰረት በማድረግም ወንጀሉን ለመከላከል አሰራርን ማዘመንና የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ያስችላል ተብሏል። የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ጠንካራ መሆንም ወንጀሉን ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

Exit mobile version