Site icon ETHIO12.COM

ቅዱስ ሲኖዶስ ኦርቶዶክስ የአስታራቂነት ሚናዋን እንደምትወጣ ገለጸ

በሀገሪቱ የተከሰተውን የሰላም እጦት በዘላቂነት ለመፍታት እና ዜጎች በሀገራቸው ተረጋግተው መኖር እንዲችሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአስታራቂነት ሚናዋን እንደምትወጣ ገለጸች።

ከግንቦት 10 እስከ ግንቦት 25/2014 ዓ.ም ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።

የጉባዔውን ቆይታ አስመልክቶም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ መግለጫ ሰጥተዋል።

ፓትርያርኩ በመግለጫቸው ሲኖዶሱ በቤተክርስቲያኗ እና ሀገራዊ የሰላም ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መምከሩን እና ውሳኔዎችን ማሣለፉን አብራርተዋል።

ለቀጣይ ሶስት ዓመታት ቤተክርስቲያኗን የሚያስተዳድሩ ቅዱሳን አባቶችን የሰየመው ሲኖዶሱ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን ደግሞ የቅዱስ ሲኖዶሱ ፀሐፊ አድርጎ መሠየሙን ብፁዕነታቸው አብራርተዋል።

ሲኖዶሱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ በተለይም በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች እየተፈፀመባት ያለውን የስርአተ አምልኮ መስተጓጎል ችግር አስመልክቶ በጥልቀት መወያየቱን ገልጸዋል።

በቤተክርስቲያኗ እና አገልጋዮቿ ላይ እየደረሰ ያለው ወከባ እንዲቆም እና አጥፊዎች ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸውም ቤተክርስቲያኗ ጠይቃለች።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው ለችግሩ መፍትሄ ለማፈላለግ ከሲኖዶሱ ጋር መወያየታቸውን በመግለጫቸው ገልጸዋል።

የክህነት አሰጣጥን አስመልክቶ ምልአተ ጉባኤው መምከሩን እና ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል፡፡

ከቤተክርስቲያኗ ተገልሎ የነበር ግለሰብ በጠየቀው መፀፀት ምህረት እንደተደረገለትም ብፁዕነታቸው አስገንዝበዋል። በትግራይ ክልል ስለ አለው የቤተክርስቲያኗ ሁኔታም ቅዱስ ሲኖዶሱ መወያየቱን በመግለጫው አብራርተዋል።

በሀገራቸው በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ለተጎዱ ወገኖችም ቤተክርስቲያኗ እንድትደግፍ መወሰኑንም አቡነ ማቲያስ በመግለጫቸው ገልጸዋል።

(አሚኮ)

Exit mobile version