Site icon ETHIO12.COM

ግብርና ሚኒስቴር በአማራና አፋር ክልሎች ድጋፍ ሰጠ


ግብርና ሚኒስቴር በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ የተጎዱ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት የፕሮግራም ወረዳዎችን ለማጠናከር እና የመፈጸም አቅማቸውን ለማሳደግ የሚያግዝ የተሸከርካሪና የቢሮ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ የተገኙ ሲሆን በጦርነቱ ለተጎዱ 54 የአማራ እና 21 የአፋር የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት የፕሮግራም ወረዳዎች ከአለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ 75 የመስክ ተሸከርካሪዎችን እና የቢሮ ቁሳቁሶችን ሲያበረክቱ እንደገለጹት ግብርና ሚኒስቴር ከዚህ በፊት ከገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም እና ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን በፕሮግራሙ ለሚደገፉ ወረዳዎች ከ468 በላይ ላንድ ክሩዘር ተሸከርካሪዎችን እና ከ3‚590 በላይ የሞተር ሳይክል ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታው አክለውም የድጋፉ አላማ በዝናብ እጥረት ምክንያት የምግብ ዋስትና ችግር ላለባቸው ወገኖች ምርት አምርተው የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ከማድረግ ባሻገር በጦርነቱ ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ የማስፈጸም አቅማቸውን ለማሳደግ ያሰበ ድጋፍ ነው ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል የግብርና ቢሮ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንግስቱ ድልነሳው አየለ እና የአፋር ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባባሪያ ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሃመድ ሁሴን ክልሎቹን በመወከል ድጋፉን የተረከቡ ሲሆን ግብርና ሚኒስቴር በክልሎቹ በነበረው ጦርነት ለተጎዱ ወረዳዎች ከገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራምና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እያደረገ ባለው ድጋፍ በምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ ያለውን ህብረተሰብ ኑሮ እንዲሻሻል ከማገዝ ባሻገር የጤና፣የመሰረተ ልማትና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በመደገፍ እየሰጠ ላለው ፈጣን ምላሽ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም የተደረገው የተሸከርካሪና የቢሮ ቁሳቁስ ድጋፍ ለታለመለት አላማ እንዲውል አቅጣጫ በመስጠት የርክክብ ስነስርአቱ ተጠናቋል፡፡
መረጃ የግብርና ሚኒሰቴር ነው

Exit mobile version